ለአማራ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ማኔጅመንት አባላት በእቅድ ዝግጅት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ስልጠና ተሰጠ
ባህርዳር፣ መጋቢት 07/2018 (አማራ ክልል ጠ/ፍ/ቤት)
ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማኔጅመንት አባላት በእቅድ ዝግጅት፣ እቅድ አፈጻጸም፣ ሪፖርት አቀራረብ፣ እንዲሁም የመሪነት ጥበብ ላይ ስልጠና ተሰጧል።
ስልጠናውን የሰጡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ ናቸው።
አቶ ፍሬው፣ የእቅድ ዝግጅት አስፈላጊነት፣ የጠንካራ እቅድ መገለጫዎች፣ እቅድ ለማዘጋጀት መነሻ ምክንያቶችን፣ የእቅድ ዝግጅት ሂደቶች፤ የመረጃና ሪፖርት ምንነት እና ልዩነት፣ የመረጃ አይነቶች፣ አስፈላጊነት የጥሩ መረጃ ባህርያት፣ የሪፖርት ምንነት፣ ይዘት እና አቀራርብ ላይ ስልጠናውን ሰጠዋል።
ከባህሪ፣ አመለካከት፣ ችሎታ፣ እውቀት፣ ልምድ እና ልዩ ብቃት አንጻር አንድ መሪ ሊኖረው ስለሚገባው የመሪነት ጥበብ ለማኔጅመንት አባላቱ ዝርዝር ገለጻ ያቀረቡት አቶ ፍሬው ፣ ወቅታዊውን የአለም፣ የሀገር ፣ የክልል እና የተቋሙ አሁናዊ ቁመና ታሳቢ በማድረግ፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን በመለየት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይዞት የተነሳውን የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ እቅድ ከግብ ለማድረስ ሁሉም አመራርና ፈጻሚ በየስራ ሂደቱ ከተቋሙ የሚቀዱ የሂደት እቅዶችን በጥራት በማዘጋጀት፣ ለተፈጻሚነታቸው በሙሉ አቅም በመስራት እና የተሰሩ ስራዎችን አጭር እና ግልጽ በሆነ አግባብ በሰዓቱ ሪፖርት በማድረግ ለጋራ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
በቀረበው ስልጠና ላይ የማኔጅመንት አባላቱን ያወያዩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፣ የቀረበው ስልጠና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የያዛቸውን የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች አንድ ባንድ በተቀመጠላቸው የጊዜ ቅደም ተከተል ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸው፣ ሁሉም የስራ ሂደት ሀላፊዎች እና ዳይሬክተሮች ከተቋሙ የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ እቅድ የተቀዳ የሂደት እቅድ በጥራት እንዲያዘጋጁ ፣ ይሄንንም የክፍል ፈጻሚዎቻቸው እንዲያውቁት፣ ለተግባራዊነቱም ሁሉም አመራርና ፈጻሚ በሙሉ አቅሙ የተጣለበትን ተቋማዊ ሀላፊነት በእኔነት ስሜት፣ በአግባቡ እና በቅንነት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ችግሮችን የለዩ፣ መፍትሄዎችን ያስቀመጡ እና የተፈጻሚነት ወሰናቸው በግልጽ የተቀመጠ እቅዶች ሊኖሩን ይገባል ያሉት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፣ የሚዘጋጁ እቅዶች የጋራ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ፈጻሚ የራሱን እቅድ ማቀድ አለበት ያሉት ክቡር ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ የክፍሉ ሀላፊዎችና ዳይሬክተሮችም ፈጻሚዎቹን በአቀረቡት እቅድ መሰረት በአግባቡ መመዘን እና መገምገም ይኖርባቸዋል ብለዋል።