ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 24/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው፣ የክልሉን ፍርድ ቤቶች 2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት አቅርበዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የተወሰደ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ እቅድ ከመታቀዱ በተጨማሪ በየደረጃው ያሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶችም በተመሳሳይ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እቅድ ጋር የሚናበብ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እና ዓመታዊ እቅድ እንዲያቅዱ ተደርጎ ወደ ሥራ የተገባ ስለመሆኑ ክቡር ፕሬዝደንት አቶ አለምአንተ አግደው ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ሪፖርቱ ገልጸዋል፡፡
የሥራ ተነሳሽነትን ፣ ትጋትን እና የሙያ ሥነ-ምግባርን በማሻሻል የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ በባለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው 438 ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ፍርድ ቤቶች የእውቅና እና ማበረታቻ መስጠት፣ እንዲሁም የጋራ ርዕይ ለመያዝ እና አቅም ለመገንባት በማለም 2185 የሚሆኑ የፍርድ ቤት አመራሮች፣ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የተሳተፉበት የዳኞች ኮንፍረንስ የሚጠቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።
የዳኝነት ነጻነት ለማረጋገጥ በፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 297/2017 መሰረት የዳኞች የሕግ ከለላ መረጋገጡ የዳኝነት ነጻነትን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና መጫወቱን የገለጹት ክቡር ፕሬዘዳንቱ፣ የዳኞችን የላቀ ሥነ ምግባር ለማረጋገጥ እና ተጠያቂነትን ከማምጣት አኳያ የዲሲፕሊን ደንብ በማውጣት እና የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት የተሰሩ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ፍ/ቤቶች የሥራ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓትን በመዘርጋት፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን እና የችሎት ሥርዓት መመሪያ በማውጣት ውሳኔ የሚያገኙ መዛግብት ብዛት በመጨመር፣ የማጥራት አቅምን በማሳደግ እና የመዛግብት የመጨናነቅ ምጣኔን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመስራት በአጠቃላይ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡ መዛግብት 94.46 ከመቶ ለሆኑ መዛግብት እልባት በመስጠት ከፍተኛ የሆነ አፈጻጸም መመዝገቡን በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሳደግ ለዳኞች የሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር የትምህርት እድል እንዲያገኙ፣ በተለያዩ የውጪ ሀገራት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ከመደረጉ ባሻገር፣ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች የሕግ ውይይት በማድረግ ጥራት እና ተገማችነት ያለው ውሳኔ ለመስጠት ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የእውቀት አስተዳደር ቋት እና ዲጂታል ላይብረሪ አገልግሎት መተግበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ከውጤት አንጻርም ጥራት ያለው ውሳኔ ሰጭነትን ለማሳደግ የታቀደው እቅድ በተሻለ ሁኔታ የተፈጸመ ስለመሆኑ ተገልጿል።
ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተደራሽ፣ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት የተላበሰ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በክልሉ ፍርድ ቤቶች ሰፊ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች መሰራታቸውን ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው የገለጹ ሲሆን፣ የስማርት ኮርት፣ ኢ- ፋይሊንግ፣ ድምጽን ወደ ጽሁፍ መቀየር፣ የጥሪ ማዕከል፣ ድረ -ገጽ፣ የደብዳቤ ሥርዓት እና የመሳሳሉት የተሰሩ ሥራዎች በዝርዝር ተገልጸዋል። ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጨማሪ በሁሉም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ በ27 ወረዳ ፍርድ ቤቶች እና በባሕር ዳር እና እንጅባራ ማረሚያ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ስራዎች መሠራታቸው ተገልጿል።
ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢ -ፋይሊንግ ሲስተም በመጠቀም 16,606 መዛግብት የተከፈቱ ሲሆን ከአሜሪካን አገር ጆርጂያ ግዛት እና ሜሪላንድ ግዛት ምስክርነት ቃል መስጠት የቻሉትን ጨምሮ 2,564 ተገልጋዮች በስማርት ችሎት ወይም እርቀት ክርክር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ብር 51,280,000 (ሃምሳ አንድ ሚሊዬን ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ) ወጪ ከማውጣት ታድጓቸዋል፡፡
ተገልጋዮች ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የሞባይል መተግበሪያ እና የተቋሙን ድረ- ገጽ በመጠቀም እንዲሁም በ 6152 የጥሪ ማእከል አማካኝነት መረጃ የሚያገኙበት አግባብ የተዘረጋ መሆኑ ተገልጿል።
አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ከማስፋት አንፃር የተሰሩ ስራዎችን በሪፖርታቸው ያቀረቡት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ የሆኑ ዘላቂ በሆነ ሁኔታ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሰረት በጥናት ለተለዩ 15 የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጠት መቻሉን፣ 538 ሴቶች የሆኑበት የ7381 የባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች ምርጫ መደረጉን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በ 1377 ቀበሌዎች ውስጥ ሥራ ማስጀመር መቻሉን፣ በግንቦት እና በሰኔ ወር ብቻ 1195 መዛግብት ቀርበው ለ1048 መዛግብት እልባት መስጠት መቻሉ ተገልጿል።
በዚህም 29,943,887 ብር ወጪ መቀነስ መቻሉ ተገልጿል። በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓት በማጠናከር 2485 መዛግብት በስምምነት መቋጨት መቻሉ ተገልጻል፡፡
የቅንጅት ሥራዎችን በማጠናከር የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እና አያያዝ የተሻለ ለማድረግ እና በሌሎች በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ እቅድ በማውጣት ሰፊ ሥራዎች ለመሥራት መቻሉ ተገልጿል።
ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ የሆነውን የክልሉ የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲቲዩት ለማጠናከር እና የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ለማስቻል የተሰሩ ሥራዎች በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
የፍርድ ቤቶች የሰው ሃብት ልማት እና ተቋማዊ ግንባታ፣ ምቹ የሥራ ከባቢ ከመፍጠር አንጻር በዞን ከፍተኛ እና ወረዳ ፍርድ ቤቶች የተሰሩ ሥራዎች፣ የሕግ ግንዛቤ እና ማኅበረሰብ ተሳትፎ ማሳደግ፣ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽነት፣ የተጋላጭ የማህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችን እና ሌሎች ጉዳዮች በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ ፍርድ ቤቶች መኖር ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ተገማች፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ፍትሃዊ እና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት፣ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አይተኬ ሚና ያላቸው መሆኑን ክቡር ፕሬዘዳንት አቶ አለም አንተአግደው ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ላነሷቸው ጥያቄዎችም ክቡር ፕሬዝደንቱ ምላሽና ማብራሪያ ሰጠዋል።


