ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ፕሮጀክቶች

በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች

የፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን መዘርጋት

በየትኛውም ጊዜ፣ አካባቢ እና ኅብረተሰብ እንደሚኖረው ሁሉ በአማራ ክልልም ሰዎች እና ቡድኖች በግላዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲደርጉ አንዱ ከሌላው ጋር በሚያደረጋቸው መስተጋብሮችና ግንኙነቶች አለመግባባቶች እና ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ የክልሉ ኅብረተሰብም አለመግባባቶች እና ግጭቶች እንዳይከሰቱ የሚከላከልበት፣ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመቆጣጠር ወይም ባሉበት ለመያዝ እና ለመፍታት የሚችልባቸው ልዩ ልዩ ባሕላዊ እና ዘመናዊ ሥርዓቶች አሉት፡፡ የክልሉ ፍርድ ቤቶችም ኅብረተሰቡ የተሟላ ፍትሕ እንዲያገኝ ዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ከሚሰጡት መደበኛና የዘወትር የፍትሕ አገልግሎት በተጨማሪ በክልሉ ያሉ ልዩ ልዩ የባሕል ፍርድ ቤቶችን እና ሌሎች አማራጭ የአለመግባባት መፍቻ ዘዴዎችን በመደገፍና በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ረገድ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባሕል ፍርድ ቤቶች ጋር በተያያዘ እየተገበራቸው ካሉ በርካታ ተግባራት ሌላ እንደ ማግባባት/መደራደር (Negotiation)፣ አስማሚነት (Mediation)፣ ማስታረቅ (Conciliation) እና የግልግል ዳኝነት (Arbitration) የመሳሰሉ ዘመናዊ አማራጭ የአለመግባባት መፍቻ መንገዶችን ከፍርድ ቤቶች ጋር በማስተሳሰር ፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች (Court-connected or court-annexed ADR) እንዲዘረጉና የተቀናጀ የፍትሕ አሰጣጥ እንዲዳብር እየተጋ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት ከፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች (Court-connected or court-annexed ADR) መካከል የፍርድ ቤት-መር አስማሚነት (Court-connected or court-annexed mediation) የሚመለከት መመሪያ አውጥቶ በተወሰኑ የተመረጡ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የሙከራ ትግበራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት በመሥራት ላይ ይገኛል::

የአስማሚነት አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን ፍርድ ቤት-መር አስማሚነት በፍትሕ አስተዳደር በተለይም በፍትሐ ብሔር ፍትሕ አስተዳደር አለመግባባቶችንና ክርክሮችን በአጭር ጊዜ፣ ያለብዙ ውጣ ውረድ፣ እንግልትና ወጭ፣ በራስ ባለቤትነትና ወሳኝነት አነታራኪ ጉዳዮችንና ከዚሁ ጋር የሚገናኙ ነገሮችን በሰላም በመነጋገር፣ አንዱ የሌላኛውን ወገን ፍላጎት፣ ጥቅም፣ መብት፣ ሁኔታ፣ አረዳድ፣ አተያይና የመሳሰሉ ጉዳዮች በመረዳትና በማወቅ፣ ለክርክር ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በገለልተኛ አስማሚ አሳላጭነትና ከአድሎና ወገንተኝነት የራቀ ድጋፍ አማካይነት ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡ በግል መጠበቅ የሚገባቸውን ምሥጥሮች ይዞ በማስቀረት፣ በክርክር ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጓዳኝ የአእምሮና የሞራል ጉዳቶች በማስቀረት ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት እድል የሚከፍት ነው፡፡ የሚፈርስ ቤተሰብን የሚታደግ፣ በክርክር ሂደት በረጅም የክረክርና የማስረጃ አቀራረብ፣ በጊዚያዊ እግድ፣ በልዩ ልዩ ሕጋዊ የሆኑና በሰበብ-አስባብ ሊቀርቡና ሌላኛውን ወገን ለብስጭት፣ ለልዩ ልዩ ጉዳቶች በማጋለጥ የተበዳይነት ስሜትንና በቀል ማርገዝን የሚያስቀር ጤነኛ የሆነ ጉርብትናን፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማስቀጠል የሚያስችል፣ የፍርድ ቤት የጉዳይ ክምችትን ከመቀነስና ክርክርን በወቅቱ ከመቋጨት ያለፈ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት የአለመግባባት መፍቻ መንገድ ነው፡፡

Your Heading

የአብክመ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት

በአማራ ክልል የህግ የበላይነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲረጋገጥ፣ ፍትህ እንዲሰፍንና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ለማድረግ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲፋጠን የዳኝነት እና የፍትህ ተቋማት ሚና በእጅጉ የጎላ ነው፡፡ እነዚህ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ማለትም ፍርድ ቤት፤ ፍትህ ቢሮ፤ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን/ በየተቋማቱ ማቋቋሚያ ህጎቻቸው ተዘርዝሮ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት ማከናወናቸውን እንደተጠበቀ ሆኖ ለጋራ ግብ በሚያገናኟቸው ጉዳዮች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፍትህ ስርዓቱ በተለይም ደግሞ የወንጀል የፍትህ አስተዳደር ሂደቱ በእነዚህ ተቋማት የሚያልፍ በመሆኑና የአንዱ ተቋም ስራ ለሌላኛው ተቋም እንደመነሻ ሊያገለግል የሚችል በመሆኑ ስራው በራሱ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትህ አካላት የትብብር መድረክ በአዲስ መልክ በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም የተመሰረተና ማስተባበሪያ ጽ/ቤትም በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስር የተደራጀ ሲሆን፣ የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት በጋራ የሚሰሩባቸውን ዘርፎች በመለየትና አሰራር ስርዓታቸውን በማስቀመጥ የስምምነት ማስተግበሪያ ቻርተር በመፈራረም ወደስራ ገብተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የክልሉ መንግስት በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባው ካጸደቃቸው አዋጆች መካከል የክልሉን ፍርድቤቶች ለማጠናከር ባወጣው አዋጅ ቁጥር 297/2017 በአንቀፅ 5 ስር የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት የዳኝነት እና የፍትህ አካላት የትብብር መድረክን እንዲያደራጅ እና እንዲያስተባብር ሥልጣን የሰጠው ሲሆን፣ በትብብር እና በቅንጅት ሊሰሩ ስለሚችሉ ስራዎችም በአንቀጽ 10 ስር እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡ በዚህ አግባብ የትብብር ሥራው እስከ ወረዳ ድረስ ተዘርግቶ እየተሰራበት ይገኛል፡፡

የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት

በ“አማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 297/2017” አንቀጽ 5(8) ስር የባሕል ፍርድ ቤቶች ዕውቅና አግኝተው እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ እና ይህንኑ ተግባር የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበላይነት ይዞ እንዲሠራ ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ የ“የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ዕውቅና ለመስጠት የወጣ አዋጅ ቁጥር 298/2017” እና አዋጁን ለማስተግበር የሚያስችል “የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች አዋጅን ለማስተግበር የወጣ መመሪያ ቁጥር 23/2018” ወጥቶ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ፡፡ የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ዕውቅና ለመስጠት በወጣው አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ መሰረት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሚመራ የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የተደራጀ የአማካሪ ምክር ቤቱ ጽ/ቤት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤትም የባሕል ፍርድ ቤቶችን በተመለከተ የሚሰጡ ሥልጠናዎችን ይለያል፣ ያስተባብራል፤ የባሕል ፍርድ ቤቶችን በሚመለከት የሚደረጉ የሚዲያ ሥራዎችን ያስተባብራል ፣ ይመራል፤ የዞን እና የወረዳ አማካሪ ምክር ቤቶችን እንቅስቃሴ ይከታተላል፣ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፤ አማካሪ ምክር ቤቱ የተወያየባቸውን ጉዳዮች እና የተሰጡ ውሳኔዎችን አደራጅቶ ይይዛል፣ ያስተገብራል፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ተቀብሎ ያደራጃል፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሪፖርት አካል ሆኖ እንዲካተት በማድረግ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲላክ ያደርጋል፤ የባሕል ፍርድ ቤትን ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት የወጣውን አዋጅ በማስተግበር ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየለዬ መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተለይም ከአማካሪ ምክር ቤት አባል ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል፤ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር የሚያስችል የአይነት እና የገንዘብ ድጋፎችን ያሰባስባል፣ ያስተዳድራል፡፡


English