ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የፕሬዘዳንቱ መልክት

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

ክቡር አቶ አለማንተ አግደው

በዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ፍ/ቤቶች ሶስተኛ የመንግስት አካል ናቸው፡፡ ዋና ተልዕኳቸውም ነጻና ገለልተኛ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው። ይህንን ትልቅ ሃላፊነት ለመወጣትና ተልዕኳቸውን ለማሳካት በሰዎች መካከል በዘር፣ በፆታ፣ በማህበራዊ አቋም እና በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ልዩነት ሳይኖር በገለልተኝነት እና በፍትሃዊነት ነፃ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል። በኢትዮጵያ እስከ 1900 ዓ.ም በነበረው ጊዜ ባሕላዊ የሽምግልና የዳኝነት ስርዓት እና ፍትሃ ነገስትን ጨምሮ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሕጎችን መሰረት ያደረገ ዳኝነት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከ1900 ዓ.ም በኋላ በተለይም ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ ዘመናዊ የሕግ ሥርዓት የተጀመረ ሲሆን በ1987 ዓ.ም አዲስ የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት ተከትሎም አገራችን በምትከተለው የፌደራል ቅርፀ መንግስት አወቃቀር መሰረት የዳኝነት አገልግሎት ትይዩ ሆነው በፌደራል እና በክልል በተቋቋሙ ፍ/ቤቶች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የክልል ፍ/ቤቶች በክልል ሕገ-መንግስት በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት በክልል ጉዳዮች ላይ እና በፌደራል ሕገ-መንግስት በተሰጣቸው ውክልና ደግሞ በፌደራል ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ስልጣን አላቸው። የአማራ ክልል ፍ/ቤቶች በፌደራል ሕገ-መንግስት፣ በ1987 በወጣዉ እና በ1994 ዓ.ም በተሸሻለዉ የክልል ህገ-መንግስት እና በተለያየ ጊዜ በወጡ ዝረዝር የሕግ ማዕቀፎች የተሰጣቸውን ነፃ የዳኝነት አገልግሎት የማረጋገጥ ተልዕኮ ለመወጣት ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህም ከ30 አመት በላይ ባስቆጠረ የዳኝነት አገልግሎት ሂደት የክልሉ ፍ/ቤቶች በዳኝነት ጥራት እና የላቁ ዳኞችን በማፍራት ይታወቃሉ። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይህንን የክልሉን ፍ/ቤቶች ጥንካሬ ለማስቀጠልና አቅማቸውን ይበልጥ ለማሳደግ፤ እንዲሁም በሂደት የታዩ ክፍተቶችን በአግባቡ በመሙላት ለሕብረተሰቡ የተሻለ የዳኝነት አገልልግሎት ለመስጠት ይቻል ዘንድ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ፍ/ቤቶች ሰፊ የለውጥ ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች እንዲተገብሩ አድርጓል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም በሃገር ደረጃ ተምሳሌት ለመሆን እና በመካከለኛ እና ረጅም ጊዜ ደግሞ በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ ተጠቃሽ ፍ/ቤቶችን ለመገንባት ራዕይ አንግቦ የተለያዩ ስትራቴጅዎችን በመቅረፅ እየሰራ ይገኛል ። በዚህም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ (በ2017 ዓ.ም) ብቻ አግልገሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጅ በማስደግፍ፣ ምቹ የማስቻያ እና የሥራ ቦታዎችን በመፍጠር፣ የዳኞች ያለመከሰስ የህግ ማዕቀፍ እንዲወጣ ማድረግን ጨምሮ፣ የፍ/ቤቶችን ነፃነት የሚጋፉ የኮሚቴ አደረጃጀቶችን በማስቀረት፣ በፍ/ቤቶች በራሳቸው እና በምክር ቤቶች ብቻ የሚመሩ በማደረግ የዳኝነት ነፃነትን ለማስከበር የሚረዱ ወሳኝ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፍ/ቤቱ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች ዘላቂነት የሚያረጋግጡ እና ተቋማዊ የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፎች እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ የባህል ፍ/ቤቶችን ማቋቋምን ጨምሮ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን የሚያጠናክሩ እርምጃዎችም ተወስደዋል፡፡ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ከዳኝነት አካሉ አልፎ አጠቃላይ የክልሉን የፍትህ ሥርዓት ውጤታማ ለማድረግ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የትብብር መድረክን (Joined Up Justice Forum) የሰብሳቢነት ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት አስደማሚ የሚባሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ይህም በዳኞች፣ በፍ/ቤት ሠራተኞች እና በአጠቃላይ በፍ/ቤቱ ማህበረሰብ እና በፍትህ አካላት ዘንድ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት ፈጥሯል። በተለይም በፍ/ቤቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2018 ዓ.ም ለ10 ተከታታይ ቀናት (ከመስከረም 20 እስከ 29 ) በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ “የጋራ ራዕይ ለጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት” በሚል መሪ ቃል በባህር ዳር ከተማ የተካሄደዉ እና ከ 2400 በላይ የክልሉ ዳኞች የተሳተፉበት የዳኞች ኮንፈረንስ፤ ፍ/ቤቱ የጀመራቸዉን የለዉጥ ሥራዎች እስከ ወረዳ ማድረስ የተቻለበት እና በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት የተደረሰበት ሲሆን በዳኞች እና በፍ/ቤቱ ሠራተኞች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሥራ ተነሳሽነትን የጨመረ ሆኗል፡፡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ለሰዉ ሃይል ልማት ከፍተኛ ቦታ በመስጠት በልዩ ትኩረት እየሰራ ሲሆን የክልሉ ፍትህና ሕግ ኢንስቲትዩት ለጠቅላይ ፍ/ቤት ተጠሪ ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 299/2017 እንደገና ከተቋቋመ በኋላ ይህ ተቋም በሕግና ፍትህ ጉዳዮች የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ለማስቻል የተለያዩ ስትራቴጅክ ውሳኔዎችን በመወሰን ድጋፎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የክልሉ መንግስት በ2017 እና 2018 በጀት ዓመት በአንፃራዊነት የተሻለ በጀት በመመደብ እና የፍ/ቤቱን የለውጥ ሥራዎች በሕግ ማዕቀፍ በማስደገፍ ረገድ በጎ ጅማሮዎች የታዩበት ነው። ወደፊትም በዚሁ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ ሌሎች የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ከፍ/ቤት ጋር ተቀራርበው መስራት የጀመሩበትና የተሻለ ድጋፍ ያሳዩበትም ነው። ለዚህም ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ከፍተኛ ምስጋና አለው። በቀጣይ ጊዜአት በጠቅላይ ፍ/ቤት እና በፍትህና የሕግ ኢንስቲትዩት ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የአሰራር እና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በማድረግ የተጀመሩ የለዉጥ ሥራዎችን በፅኑ መሰረት ላይ የማስቀመጥና ለተቋም ግንባታ መሰረት የመጣል ሥራዎች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የባሕል ፍ/ቤቶችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሥራ ማስጀመር እና ዘላቂነታቸዉን ማረጋገጥ፣ የክልሉን ሕዝብ የሚመጥን እና ደረጃዉን የጠበቀ አዲስ የጠቅላይ ፍ/ቤት ሕንጻ መገንባት፣ ዓለምአቀፍ የግልግል ዳኝነት ማሰልጠኛ ተቋም መገንባት፣ የሕግ የበላይትና የሰላም ማዕከል መገንባት፣ የተከላካይ ጠበቆች አገልግሎት ራሱን ችሎ እንዲደራጅ ማድረግ፣ የዲጅታላይይዜሽን ሥራችንን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ተጠቃሽ ትኩረት የሚደረግባቸው ተግባራት ይሆናሉ፡፡ ፍ/ቤታችን ያስቀመጠዉን ራዕይ ለማሳካት እና ተልዕኮዉን ለመፈጸም ከምግዜዉም በላይ በከፍተኛ ትጋትና ቁረጠኝነት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በሌላ በኩል ነፃ፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ተገማች እና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎትን የማረጋገጥ ጉዳይ በፍርድ ቤቱ ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም። ስለሆነም ሁሉም የፍትህ አካላት፣ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት፣ የሕጉ ማህበረሰብ፣ ማስረጃ ሰጭ ተቋማትን እና አጠቃላይ የማህበረሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ፍ/ቤቱ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እንዲደግፉ በራሴና በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ስም ጥሪየን አቀርባለሁ ። .
ፍትህን በታማኝነት !!
ተምሳሌት የሆኑ ፍ/ቤቶችን ለመገንባት እንተጋለን ! !
ዓለምአንተ አግደው ወንድሜነህ,
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዘዳንት
 

2
1