ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች በ2018 በጀት ዓመት 94.46 በመቶ የመዝገብ አፈጻጸም ማስመዝገባቸው ተገለጸ

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች በ2018 በጀት ዓመት 94.46 በመቶ የመዝገብ አፈጻጸም ማስመዝገባቸው ተገለጸ

ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው ለክልሉ ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ የ2018 በጀት ዓመት የፍርድ ቤቶችን አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርቱ መሠረት፣ ፍርድ ቤቶቹ ከ25 ዓመቱ የዳኝነትና የፍትሕ አካላት አሻጋሪ ዕቅድ የተቀዳውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መነሻ በማድረግ 11 ዋና ዋና ግቦችን ያካተተ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በማዘጋጀት ውጤታማ አፈጻጸም ማስመዝገባቸው ተገልጿል።

በተለይም በዓመቱ ለፍርድ ቤቶች ከቀረቡ መዛግብት 94.46 በመቶ ለሚሆኑት እልባት በመስጠት ከፍተኛ የመዝገብ አፈጻጸም መመዝገቡ ተገልጿል። ጥራት ያለው የዳኝነት ውሳኔ ለመስጠት የተዘጋጁ ፕሮግራሞችም በተሳካ ሁኔታ መፈጸማቸው ተመልክቷል።

ሪፖርቱ የዳኞችን የሙያ ብቃት ለማጎልበት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የትምህርትና የልምድ ልውውጥ እድሎች መፍጠራቸውን፣ የእውቀት አስተዳደር ቋትና ዲጂታል ላይብረሪ ሥራ መጀመሩን እንዲሁም የሥነ ምግባር ሥርዓትን በማጠናከር የዳኞች ተጠያቂነት ላይ ተጨባጭ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ያመለክታል።

በዳኝነት አገልግሎት ዘመናዊነት ረገድም የስማርት ኮርት፣ የኢ-ፋይሊንግ ሥርዓት፣ ድምፅን ወደ ጽሑፍ የሚቀይር ቴክኖሎጂ፣ የ6152 የጥሪ ማዕከል፣ ድረ-ገጽና ሌሎች ዲጂታል አገልግሎቶች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በሁሉም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ በ27 ወረዳ ፍርድ ቤቶች እና በባሕር ዳርና እንጅባራ ማረሚያ ቤቶች ተግባራዊ መደረጋቸው ተገልጿል። በዚህም ዜጎች ከየትኛውም ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን ማስኬድና መከታተል በመቻላቸው የጊዜና የወጪ ቁጠባ መፈጠሩ ተጠቁሟል።

በአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓት ማስፋፋት ረገድም 15 የባህል ፍርድ ቤቶች እውቅና ማግኘታቸው፣ 7,381 የባህል ፍርድ ቤት ዳኞች መመረጣቸው እና በ1,377 ቀበሌዎች ሥራ መጀመራቸው ተገልጿል። በግንቦትና በሰኔ ወር ብቻ 1,048 መዛግብት እልባት በማግኘታቸው 29.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ማስቀረት መቻሉም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በሪፖርቱ የፍትሕ ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅት በማጠናከር የዜጎችን መብት ለማስከበርና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸው እንዲሁም የክልሉ የፍትሕና የሕግ ኢንስቲቲዩትን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ጠንካራ ጥረቶች መደረጋቸው ተጠቅሷል።

በመጨረሻም ክቡር ፕሬዝደንቱ ፍርድ ቤቶች የፍትሕ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ለክልሉ ኢኮኖሚ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለመልካም አስተዳደር መጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በመግለጽ፣ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ዝርዝር ማብራሪያና ምላሽ  ሰጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *