ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሕ ሙዚየም ያየነው ሥራ ከክልሉ አልፎ  በሀገር ደረጃ ለብዙዎች መነሳሳት ይሆናል” — ዶ/ር በለጠ ሞላ- የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር

“በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሕ ሙዚየም ያየነው ሥራ ከክልሉ አልፎ  በሀገር ደረጃ ለብዙዎች መነሳሳት ይሆናል” — ዶ/ር በለጠ ሞላ- የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር

ባሕርዳር ፣ ነሐሴ 29/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፣ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ቢሮ ውስጥ የተገነባውን የፍትሕ ሙዚየም በጎበኙበት ወቅት ፍርድ ቤቱ በቴክኖሎጂና በዳኝነት አገልግሎት ዘርፍ ያከናወናቸውን ሥራዎች አድንቀዋል።

ዶ/ር በለጠ ሞላ፣ የፍትሕ ሙዚየሙን መጎብኘታቸው የሀገሪቱን የፍትሕ ታሪክ ለመረዳት ትልቅ ዕድል እንደሰጣቸው ገልጸው፣ በተለይም ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸው የቴክኖሎጂ ልማትና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች እጅግ የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፍርድ ቤቱ የተገበረው የቴክኖሎጂ ሥራ በሀገር ደረጃ የወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በተቋማዊ ደረጃ በምን ያህል መልኩ ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በተለይም የፍትሕ ታሪክ መዛግብትን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ የዲጂታል ዳኝነት መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት፣ ግልጽና የርቀት ክርክር የሚካሄድባቸውን ዘመናዊ የችሎት አዳራሾች መገንባት፣ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትንና የጥሪ ማዕከልን ማደራጀት የፍርድ ቤቱ የለውጥ ሥራ ዋና መገለጫዎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

“ያየሁት ሥራ የሀገር አቀፍ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በምን ያህል ደረጃ እየተተገበሩ እንዳሉ ያሳየ ነው” ያሉት ዶክተር በለጠ፣ ለዚህ የቴክኖሎጂ ዝርጋታና የታሪክ መዛግብት ዲጂታላይዜሽን ሥራ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን፣ በተለይም ከፍተኛ አመራሩን አመስግነዋል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ የተገበራቸው ወረቀት አልባ የዳኝነት አገልግሎቶችና ሌሎች የለውጥ ሥራዎች የዳኝነት አገልግሎትን ከማዘመን ባለፈ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ያየነው ሥራ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ለብዙዎች መነሳሳት እንደሚሆን አልጠራጠርም” ሲሉም ዶ/ር በለጠ ሞላ ተናግረዋል።

የፍትሕ ሙዚየሙ የተመረቀው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አረጋ ከበደ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ሲሆን፣ ከምረቃ መረሃ ግብሩ በተጨማሪ፣ የፍርድ ቤቱ የዲጂታላይዜሽን መሠረተ ልማቶች፣ ዘመናዊ የችሎት አዳራሾች፣ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትና የጥሪ ማዕከል ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ የለውጥ ሥራዎች ተጎብኝተዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዲጂታል ዳኝነት፣ በታሪካዊ መዛግብት ጥበቃና በዳኝነት አገልግሎት ማዘመን ያከናወናቸው ሥራዎች ለሌሎች የፍትሕ ተቋማት ተሞክሮ ሊሆኑ እንደሚችሉ በሥነ-ሥርዓቱ ተገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *