ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የዳኞች አስተዳደር ዐብይ ጉባኤ መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ

የዳኞች አስተዳደር ዐብይ ጉባኤ መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ

ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 19/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች አስተዳደር ዐቢይ ጉባኤ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ መክሮ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ጉባኤው ከመከረባቸው ጉዳዮች አንዱ በተለያዩ የአይ.ሲ. ቲ የሃላፊነት እና የሙያ መደቦች ላይ ተመድበው እንዲሰሩ ረጅም ጊዜ በወሰደ ጥልቅ የመለያ ሂደት ተጣርተው ያለፉ እጪዎችን ሹመት ማጽደቅ ሲሆን፣ በዚህም 12 ተወዳዳሪዎች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአይ.ሲ.ቲ ዳይሬክቶሬት ስር ተመድበው እንዲሰሩ ሹመት ሰጧል።

ጉባኤው ከዚህ በተጨማሪም፣ በይግባኝ የቀረቡለትን 8 የዲሲፕሊን እና 5 የተለያዩ ቅሬታዎችን በመመርመር ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ከቀረቡት የዲሲፕሊን ይግባኞች ውስጥ በአራት የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የስንብት ውሳኔ ሀሳብ ሰጥቷል።

አንድ በንዑስ ጉባኤ ደረጃ የስንበት የውሳኔ ሃሳብ የተሰጠበትን ጉዳይ መርምሮ በነጻ እንዲሰናበት የወሰነው ጉባኤው፣ ሌሎች ሁለት የዲሲፕሊን ጉዳዮች እንደገና እንዲታዩ ወደ ንዑስ ጉባኤ መልሷል።

በሌላ አንድ የዲሲፕሊን ጉዳይ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ማጣራት በማስፈለጉ ጉዳዩ ተጣርቶ ለቀጣይ ጉባኤ እንዲቀርብ ውሳኔ ተሰጦበታል።

ጉባኤው የዝውውር መመሪያ ማሻሻያ ጥናት እና ረቂቅ የዝውውር መመሪያ ማሻሻያ ቀርቦለት የተመለከተ ሲሆን፣ ጥናቱን እና ረቂቁን መርምሮ፣ የዝውውር መመሪያ ማሻሻያውን በማጽደቅ ተጠናቋል።

በመጨረሻም፣ የዐቢይ ጉባኤ አባላቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎች ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን፣ አገልግሎት ፈላጊው ህብረተሰብ ባለበት ቦታ ሆኖ የዳኝነት አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ የተሠራውን ሥራ አድንቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *