ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 14/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አሰጣጥ በመሰረታዊነት በማሻሻል ለሕብረተሰቡ ፈጣን፣ ወጭ እና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት በበርካታ የለውጥና የማሻሻያ ሂደቶች ላይ እያለፈ ይገኛል።
በሁሉ አቀፍ ለውጥ ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በዘመናዊ የዳኝነት መስጫ መሰረተ ልማቶች፣ በምቹ የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ግንባታ፣ በሥር-ነቀል የተቋም ለውጥ እና ማሻሻያ፣ ለአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ተገማችነት አጋዥ የሆኑ የዲጅታል ዳኝነት አገልግሎት መስጫዎች ዝርጋታ፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፈ ብዙ የተቋም አሰራር ለውጥ ትግበራዎች ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ከማሻሻል እና ከማዘመኑ ትይዩ የክልሉ እና የሀገሪቱ የፍትሕ ስርዓት ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ ለመድረስ ያለፈባቸውን ሂደቶች በጊዜ እና የታሪክ ቅደም ተከተል የሚያሳይ፣ ሀገሪቱ በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ግንባታ የተጓዘችበትን ረጅም ርቀት ለትውልዱ የሚተርክ፣ በዳኝነት ፣ በሕግ እና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ምሁራን በማጣቀሻነት የሚያገለግሉ የቁስ፣ የምስል እና የሰነድ ክምችት ያለው የፍትሕ ሙዚየምም ገንብቷል።
የፍትሕ ሙዚየሙን ጨምሮ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተከናወኑ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎች ከክልሉ አልፈው ለሌሎች ክልሎች እና መሰል የፍትሕ ተቋማት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ በርካታ መሪዎች፣ የተቋማት ሀላፊዎች እና የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች እየጎበኟቸው ይገኛሉ።
በዛሬው እለትም፣ በአፍሪካ ሕብረት የደህንነት ጥናት ማዕከል ተወካይ እና የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ዳይሬክተር ፓውል ሳይመን (ዶ.ር) እና የልኡካን ቡድናቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመገኘት የተከናወኑ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ገለጻ እና ማብራሪያ የተደረገላቸው እንግዶቹ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የስማርት ችሎት አገልግሎት፣ የዲጅታል አንድ ማእከል፣ የጥሪ ማእከል፣ የፍትሕ ሙዚየሙን እና ሌሎችን የአገልግሎት ማሻሻያ መሰረተ ልማቶች ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ መልስ አስተያየታቸውን የሰጡት ዶክተር ፓውል ሳይመን "ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው ስራዎች አስደንቀውኛል፤ በጉብኝቱ ያየኋቸው የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች እንደ አፍሪካዊ ኩራት እንዲሰማን የሚያደርጉ ናቸው" ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዲጂታላይዝድ ሆኖ ዘመኑን የዋጀና ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ለህዝቡ እየሰጠ መሆኑን አይቻለሁ ያሉት በአፍሪካ ሕብረት የደህንነት ጥናት ማዕከል ተወካይ እና የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ዳይሬክተሩ ዶክተር ፓውል ሳይመን፣ ለዚህም ክቡር ፕሬዝዳንቱንና የሥራ ባለደረቦቻቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት አፈልጋለሁ ብለዋል።













