ባሕር ዳር፣ ጥቅምት 9/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ይህንን ያስታወቀው፣ የ2019 በጀት ዓመት ይፋዊ የችሎት ማስጀመሪያ መረሃግብር ባካሄደበት መድረክ በቀረበው የ2018 በጀት ዓመት የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የአፈጻጸም ሪፖርት ነው።
ፍርድ ቤቱ የ2019 በጀት ዓመት መደበኛ የችሎት ሥራ ማስጀመሪያ፣ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ለአጋር አካላት የማስተዋወቅ መድረክ አካሂዷል።
የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ አማረ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ የፍትሕ ሥርዓቱን በመጠበቅ በአዲስ መንፈስና ብርታት ወደ ሥራ በመግባት ማኅበረሰቡን በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ገበየ ሃይሌ (ዶ.ር) በበኩላቸው፣ የፍትሕ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ማስከበርንና ሥርዓት አልበኝነት እንዳይስፋፋ መከላከልን እንደ ቀዳሚ ተግባር በመውሰድ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ ለሕግ ያለው አመለካከት እንዳይቀንስ፣ የፍትሕ ተቋማት ቀልጣፋና ታማኝነት የተላበሰ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ አቶ በሪሁን መንግሥቱ በበኩላቸው፣ የፍትሕ ተቋማት ሰላም እንዲረጋገጥና እንዲጸና፣ እንዲሁም በሕግ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የፍትሕ ተቋማት ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት መሥራትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም መፍታት እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመረሃግብሩ፣ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም፣ የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ አስቻይና ፈታኝ ሁኔታዎች ቀርበው ተገምግመዋል። በተለይም ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ ዲጂታላይዜሽንን ማስፋፋት፣ በቨርቹዋል ችሎቶች የዳኝነት ሥራን ማከናወን፣ የውሳኔ አሰጣጥ ጥራትን ማሳደግና የፍትሕ ሥርዓቱን ማጠናከር ላይ የተሠሩ ሥራዎች ቀርበዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ 83.6 ከመቶ የመዝገብ አፈጻጸም ክንውን መመዝገቡ ተገልጿል።
በተጨማሪም የሠራተኞችን ብቃት በሥልጠና ማሳደግ፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም፣ ሴቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን የነፃ የሕግ ውክልና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም ምቹ እና አስተማማኝ፣ ደሕንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢ ከመፍጠር አኳያ የተከናወኑ ስራዎች በዝርዝር ቀርበዋል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ሥራዎችና ክፍተት የታየባቸው ዘርፎች በጥንካሬና በድክመት አቅጣጫዎች ተለይተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በመጨረሻም፣ ተሳታፊዎች በቀረቡት ጉዳዮች ላይ ሐሳብና አስተያየታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ተግባራቸውን በተሻለ ሁኔታ ለፈጸሙ ዳኞች ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል።
ዘገባው የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው










