ባሕር ዳር ፣ ጥቅምት 9/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የ2019 በጀት ዓመት መደበኛ የችሎት አገልግሎቱን በይፋ የጀመረው የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በስራ ማስጀመሪያ መረሃግብሩ፣ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዳኞች፣ ሠራተኞች፣ ወረዳ ፍርድ ቤቶችና አጋር አካላት የእውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
ፍርድ ቤቱ የ2019 በጀት ዓመት መደበኛ ሥራውን በድምቀት ባስጀመረበት መርሃ ግብር ላይ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ወንድሙና ሌሎች የዞኑ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
አቶ ዮሐንስ ወንድሙ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መረሃግብሩ የተሰናዳው፣ ፍርድ ቤቶች በዳኞች የክረምት ዕረፍት ምክንያት በከፊል ዝግ ሆነው ውስን ሥራዎችን ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን በይፋ ለማሳወቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
የፍርድ ቤቱን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም በመገምገም የተገኙ ጠንካራ ጎኖችን ማጠናከር፣ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በ2019 በጀት ዓመት እንዳይደገሙ ማድረግና በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የተጀመሩትን ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሥራዎች በተግባር እንዲያሳኩ አቅጣጫ ማስቀመጥም የመረሃግብሩ ሌላው አላማ መሆኑን አብራርተዋል።
ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው የሕግ የበላይነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ተደራሽ፣ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ እንዲሁም በተገልጋዮች ዘንድ ተአማኒነትን ያተረፈ የፍትሕ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። በተለይም የአማራጭ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ለማስፋት የባህል ፍርድ ቤቶችን በወረዳዎችና በቀበሌዎች የማደራጀትና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ፣ ለአንድ ሀገር ሰላምና ዕድገት የፍርድ ቤቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩም የፍርድ ቤቶችን ሥራ ለመደገፍና የጋራ ዓላማዎችን በቅንጅት ለማሳካት በትብብር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም ክልሉ የጀመራቸው የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች በዞኑ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ እንዲተገበሩ አስተዳደሩ ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በመድረኩ የፍርድ ቤቱ የዕቅድ፣ በጀት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ሸጋው ወ/ጊዮርጊስ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምንና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን አቅርበዋል። በተመሳሳይ፣ የባህል ፍርድ ቤቶች ፎካል ፐርሰን ዳኛ አቶ ትዕዛዙ ጌታቸው በ2018 በጀት ዓመት በዞኑ የሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ያከናወኗቸውን ሥራዎች አቅርበዋል።
በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ በተካሄደ ውይይት ተሳታፊዎች አስተያይት የሰጡባቸው እና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ለተነሱት ጉዳዮችም ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል።
የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ወንድሙ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ ፍርድ ቤቱ በ2018 በጀት ዓመት ያስመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ የሚገኙ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችን በአጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ባወዳደረበት መድረክ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ደረጃ መያዙን በማሳያነት አንስተዋል።
የተገኘው ውጤትም የዳኞች፣ የሠራተኞችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የጋራ ትብብርና ቅንጅት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚሁ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ ለተመዘገበው ውጤት ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዳኞች፣ ሠራተኞችና የጉባኤ ተሿሚዎች፣ ከፍርድ ቤቱ ጋር በቅንጅት ለሠሩ አጋር አካላት እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ተቋሙን ለለቀቁ ሠራተኞች የእውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በተጨማሪም ከዞኑ 32 ወረዳ ፍርድ ቤቶች መካከል በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳ ፍርድ ቤቶች የእውቅናና የምስጋና ሰርተፊኬት ተበርክቷል።
በዚህም፣ የባሶና ወራና ወረዳ ፍርድ ቤት አንደኛ፣ የጣርማ በር ወረዳ ፍርድ ቤት ሁለተኛ እንዲሁም የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ ሆነዋል።
ዘገባው የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው










