ባሕር ዳር ፣ ጥቅምት 09/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደርና የወልድያ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመገኘት የስማርት ችሎት (Smart Courtroom) እና የቨርቹዋል ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ፣ የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ ታምራት ደምሴና የአመራር ልዑካቸው፣ የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደሱ፣ የጉባላፍቶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ በየነ፣ እንዲሁም የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ አባላት አመራሮች ተሳትፈዋል።
አመራሮቹ በጉብኝታቸው፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያደራጃቸውን ሁለት የቨርቹዋል ዳኝነት አገልግሎት መስጫ ስማርት ችሎቶችን ተመልክተዋል።
በጉብኝቱም በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው የቨርቹዋል ዳኝነት አገልግሎት በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ተገልጋዮች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የዳኝነት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ባሕር ዳር መጓዝ ሳያስፈልጋቸው፣ በዞኑ ማዕከል በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በተደራጁት ስማርት ችሎቶች አማካኝነት አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ተመልክቷል።
በዚህም መሠረት ተገልጋዮች ![]()
በኤሌክትሮኒክ ሰነድ ማቅረቢያ (e-Filing) አማካኝነት አቤቱታ ማቅረብና መዝገብ ማስከፈት፤
በቨርቹዋል ችሎት ክርክራቸውን ማቅረብ፤
የችሎት ቀጠሮዎቻቸውን መከታተል፤
የትዕዛዝ፣ የፍርድና የውሳኔ ግልባጭ ሰነዶችን በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በኩል ማግኘት፤ የሚችሉ ሲሆን፣ ይህም የተገልጋዮችን የጉዞ ወጪና የጊዜ ብክነት በመቀነስ፣ ከእንግልት በማዳንና የፍትሕ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በላስታ ወረዳ ፍርድ ቤት በ ላልይበላ ከተማ ተመሳሳይ የስማርት ችሎት አገልግሎት ያደራጀ ሲሆን፣ ይህም የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ የዲጂታል ዳኝነት አገልግሎትን በላስታና በቡግና ወረዳዎች አካባቢ ለሚገኙ ተገልጋዮች ተደራሽ ለማድረግ ዕድል የሚፈጥርለት መሆኑ ተመልክቷል።
የስማርት ችሎትና የቨርቹዋል ዳኝነት አገልግሎት መስፋፋት ፍርድ ቤቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን በመጠቀም ፈጣን፣ ተደራሽና ወጪ ቆጣቢ የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ዓይነተኛ መንገድ ነው።
ዘገባው የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።











