ባህር ዳር፣ መስከረም 20/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ “ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው በአዳዲስ ሕጎችና ወቅታዊ የዳኝነት አገልግሎት ማእቀፎች ላይ፣ በፍትሕ አገልግሎት ተደራሽነትና ቅልጥፍና፣ በዳኝነት ነፃነትና ተጠያቂነት፣ በሙያ ሥነ-ምግባር፣ በየፍርድ ቤቶች የማሻሻያ ስራዎች ላይ በጥልቀት የሚመከርበት ነው።
በጉባኤው ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፉት ሁለት ዓመታት በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያከናወናቸውን የሪፎርም ሥራዎች ጠቅሰው፣ የሥራ አካባቢን ማሻሻል፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ እና ተቋማዊ ትብብርን ማጠናከር የዳኝነት ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዳኝነት ነፃነት የዳኞች የግል መብት ብቻ ሳይሆን ዜጎች ትክክለኛና ያልተጓደለ ፍትሕ እንዲያገኙ የሚያስችል ዋስትና መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።
በዚህም የዳኝነት ነፃነት ከተጠያቂነት ጋር ተጣምሮ መጓዝ እንዳለበት፣ የሙያ ሥነ-ምግባር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ መጠናከር እንዳለባቸው አፈ ጉባኤዋ አመልክተዋል።
በተለይም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የህዝብ እምነትን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የፍርድ ቤቶችን አሠራር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስደገፍም የዳኝነት ሥርዓቱን ለማዘመንና የአገልግሎት ቅልጥፍናን ለማሳደግ የሚያግዝ በመሆኑ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
አፈ ጉባኤዋ አክለውም፣ የፍትሕ ሥርዓት የአንድ ተቋም ብቻ ኃላፊነት ባለመሆኑ ተቋማት በትብብርና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸው፣ የክልሉ ምክር ቤትም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመንና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍርድ ቤቶች ጋር በትብብር የሚሠራውን ሥራ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የዳኞች ዕውቀትና ሙያዊ ክህሎት በቀጣይነት እንዲዳብር እና ጉባኤው በየዓመቱ በወቅቱ እንዲካሄድ ማድረግ ለተቋማዊ ግንባታና ለፍትሕ ሥርዓቱ መጠናከር የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸው፣ የፍርድ ቤቱን አመራርና ሠራተኞች አመስግነዋል።
አፈ ጉባኤዋ አክለውም፣ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ጠንካራና ነፃ የዳኝነት ሥርዓት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለዜጎች መብት ጥበቃ፣ እና ለልማት አስፈላጊ መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ ዳኞች ጠንካራ፣ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ በዕውቀትና በሙያ የዳበሩ እና በሥነ-ምግባር የታነጹ መሆን እንዳለባቸው አፈ ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።
“የዳኝነት ሥራ የዜጎች የመጨረሻ ምሽግ ነው” ያሉት አፈ ጉባኤዋ፣ ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስለሚኖረው የሙያ ክህሎታቸውን በአግባቡ በመጠቀም ያለአድልዎ ፍትሕ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ለ 10 ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው 2ኛው ዓመታዊ የአማራ ክልል ዳኞች ጉባኤ፣ የዳኞችን የውሳኔ ሰጭነት አቅም ከሚያጎለብቱ ስልጠናዎች በተጨማሪ፣ ባለፈው የሥራ ዘመን የተከናወኑ ሥራዎችንና ውጤቶችን በመገምገም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን ለመወሰን የሚያግዝ መድረክ ይሆናል።





