ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች 2ኛ ዓመታዊ ጉባኤ በይፋ ተጀመረ

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች 2ኛ ዓመታዊ ጉባኤ በይፋ ተጀመረ

ባሕር ዳር፣ መስከረም 20/ 2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለማላቅ በማሰብ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 297/2017 የሕግ መሠረት ያለው ነው።

በዛሬው እለት ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

በእለቱ የጉባኤውን አላማ አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ጉባኤው ዳኞች በፍትሕ ሥርዓቱ ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ የሚይዙበት፣ ትኩረት በሚሹ የዳኝነት አገልግሎቶች ላይ የተቀራረበ አረዳድ እንዲኖራቸው የሚያደርግ፣ በአዳዲስ እና በተሠጡ የህግ ጉዳዮች ላይ የዕይታ አድማሳቸውን የሚያሰፉበት እና የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን የተሟላ እና የላቀ ለማድረግ በማለም የሚዘጋጅ መሆኑን ገልጸዋል።

የመጀመሪያው ጉባኤ የጋራ ርዕይ ፣ ለጠንካራ የዳኝነት አገልግሎት በሚል መሪ ቃል የተከናወነ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዝደንቱ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከምን ጊዜም በላይ የተሻለ እንደነበር እና በክልሉ ምክር ቤት እውቅና የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል። ለዚህም የፍርድ ቤቱን ዳኞች እና መላ ሠራተኞች አመስግነዋል።

የዳኝነት ነጻነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ ተሰጧቸው ከተሰሩ ሥራዎች መካከል መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ አለምአንተ፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ጀምሮ በከፍተኛ እና ወረዳ ፍርድ ቤት ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር የተሠራ ስራ ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል።

የተከራካሪ ወገኖችን ጊዜ፣ ገንዘብ እና እንግልት የሚቀንስ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተሠራው የዲጂታላይዜሽን ሥራ በክልሉ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በሥነ- ምግባር ግንባታ፣ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ሥራዎች በጥቂቱ የሚገለጹ የተከናወኑ ሥራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ25 አመቱን የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ዕቅድ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የዘርፉ ቀጣይ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው የክልሉ ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ መካሄድ በፍርድ ቤቶች ሁሉአቀፍ የለውጥ ስራዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የዘንድሮው ጉባኤም፣ የተጀመሩ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል በሚችሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይካሄዳል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *