ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የባሕል ፍርድ ቤቶች ዳኞችን አቅም መገንባት የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ

የባሕል ፍርድ ቤቶች ዳኞችን አቅም መገንባት የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ

ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 27/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ (CRS) እና ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባሕር ዳር–ደሴ ሀገረ ስብከት (CCE-BD) ጋር በመተባበር ለባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች አሰልጣኞችና ሽማግሌዎች የስድስት ቀናት የአቅም ግንባታ ሥልጠና ጀምሯል።

በስልጠናው መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ወርቁ ያዜ (ረ/ፕ) ፣ የባሕል ፍርድ ቤቶች ፈጣን፣ ተደራሽ እና ወጪ ቆጣቢ የፍትሕ አገልግሎት በመስጠት እና ዘላቂ ሰላማዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። እንዲሁም የሴቶችና የሕፃናት መብቶችን ጨምሮ ሰብአዊ መብቶችን እንዲሁም በባሕል ፍርድ ቤቶች አዋጅ የተመለከቱ መሰረታዊ መርሆዎችን አስመልክቶ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር የሚሰጡ ስልጠናዎችን መደገፍ የሁሉም አጋር ተቋማት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ ፓስቶራል ኮርዲኔተርና የባሕር ዳር–ደሴ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አባ ታምራት አቶ በበኩላቸው፣ አለመግባባቶችን በእርቅና በስምምነት መፍታት የማኅበረሰብን አንድነት እንደሚያጠናክርና የባሕል ፍርድ ቤቶችን ማጠናከር ፈጣን ፍትሕን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በስልጠናው የመጀመሪያ ቀን የባሕል ፍትሕ ሥርዓት፣ የሕግ ብዝኃነት፣ መሠረታዊ መርሆዎች፣ የዳኝነት ነፃነት፣ የባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች ሚናና ኃላፊነት፣ ሰብአዊ መብቶች፣ የጾታ እኩልነት እና የባሕል ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት በሚመለከቱ ርዕሶች ላይ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ስልጠናውን የሰጡትም፣ የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ይማም ሰይድ እና የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ ተመራማሪ እና አሰልጣኝ አቶ አበበ ካሴ ናቸው፡፡

በክልሉ ውስጥ ለ15 የባሕል አለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች እውቅና በመስጠትና በ1,377 ቀበሌዎች የባሕል ፍርድ ቤቶችን በማደራጀት የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሠራ ሲሆን፣ የተጀመረው ስልጠና የባሕል ፍርድ ቤቶችን አቅም በማጠናከር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *