ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ማጠቃለያ እና  የቀጣይ ዓመት የትኩረት መስኮች ውይይት ተካሄደ

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ማጠቃለያ እና  የቀጣይ ዓመት የትኩረት መስኮች ውይይት ተካሄደ

ባሕርዳር ፣ ነሐሴ 05/2018(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች፣ ዳኞች፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሁሉም ምድብ ችሎቶች አስተባባሪዎችና ዳኞች በተገኙበት የክልሉ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም የማጠቃለያ መድረክ እና የቀጣይ በጀት ዓመት የትኩረት መስኮች ላይ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ፣ የ2018 ዓ/ም የፍርድ ቤቶች እቅድ አፈጻጸም፣ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ እና የ2019 ዓ/ ም የትኩረት አቅጣጫዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢ ፣ ግልጽ፣ ፈጣን እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ያለመ መሆኑ በቀረበው ሪፖርት የተገለጸ ሲሆን፣ በሶስት ዙር ትግበራ የክልሉን ፍርድ ቤቶች ዲጂታላይዝ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ትግበራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በሁሉም ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በ27 ወረዳ ፍርድ ቤቶች እና በሁለት የማረሚያ ቤቶች መተግበር የተቻለ መሆኑ ተገልጿል።

የመረጃ ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የፍርድ ቤት ኔት ወርክ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑም ተገልጿል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት በቢሯቸው ሆነው የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የወረዳ ፍርድ ቤቶችን አሰራር መከታተል የሚችሉበት ስርዓት የተዘረጋ መሆኑም በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል።

የስማርት ኮርት፣ ኢ- ፋይሊንግ፣ ትራንስክሪፕሽን፣ የሞባይል መተግበሪያ እና ድረ ገጽን ጨምሮ ዲጅታል ፊርማ፣ ዲጅታል አንድ ማዕከል እና የጥሪ ማዕከል አገልግሎቶች ከተተገበሩት እና ሥራ ላይ ከዋሉት የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫዎች መካከል ተጠቅሰዋል።

በ2018 ዓ.ም በነበረው እቅድ አፈጻጸም የዳኝነት አገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍና ከመቸውም ጊዜ በላይ ማሻሻል የተቻለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የክልሉ ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን አመላካች ነው።

የተለያዩ ቅጾችን በማዘጋጀት እና ለባለጉዳዮች በነጻ በማቅረብ ከ209 ሚሊየን ብር በላይ ባለጉዳዮች ሊያወጡ የሚችሉትን ወጪ ማዳን መቻሉም ተገልጿል።

ከቀረቡት የአፈጻጸም እና የቀጣይ ዓመት መነሻ እቅዶች በመነሳት አመራሮች፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶች፣ የምድብ ችሎት አስተባባሪዎችና ዳኞች በበጀት ዓመቱ አፈጻጸም፣ በቀጣይ ዓመት የትኩረት መስኮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን የላቀ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ ማእከል ለማድረግ መወሰድ ባለባቸው የቀጣይ አመት ተግባራት ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸው እና በየደረጃው ባሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የተተገበሩ ሥራዎች የሚታዩ እና ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ መሆናቸውን የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች፣ ሊሻሻሉ ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የዲጅታላይዜሽን መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ምቹ የስራ ከባቢ ለመፍጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ የዳኞችን አቅም ለመገንባት እየተካሄዱ ያሉ መደበኛ የዳኞች ውይይቶች፣ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች፣ የልምድ ልውውጦች እና ሌሎችም አሰራሮች የክልሉ ፍርድ ቤቶች የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገባቸው አጋዥ መሆናቸውን የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፣ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያይቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በበኩላቸው፣ የተጀመሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ በችግርነት የተነሱት ደግሞ በሂደት እንደሚፈቱ ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ፣ መንግስትና ሕገ መንግስቱ የሰጠንን ሀላፊነት እና አደራ በአግባቡ በመወጣት በአገልግሎት አሰጣጣቸው አርአያ የሆኑ ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት የያዝነውን እቅድ እውን በማድረግ ተገልጋዩ የሚተማመንባቸው የዳኝነት ተቋማትን መገንባት አለብን ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *