ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ለማሻሻል የተሰጠን አደራ እና ኃላፊነት ነው”  ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ለማሻሻል የተሰጠን አደራ እና ኃላፊነት ነው”  ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው

ባሕር ዳር፣ ነሀሴ 05/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ማጠቃለያ እና የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በእለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ታቅዶ ሲሰራበት የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

በመደበኛ ፍርድ ቤቶችም ሆና በአማራጭ አለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች ውጤታማ ሥራ የተሰራበት ጊዜ መሆኑን ያስታወቁት ክቡር ፕሬዝደንቱ ፣ ይሕም የክልሉን ምክር ቤት ጨምሮ የተለያዩ አካላት እውቅና የሰጡት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ.ር) ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በጎበኙበት ወቅት የተሰራው ስራ ተስፋ ሰጪ መሆኑ መግለጻቸው እና በአጭር ጊዜ ለተገኘው ውጤት የሰጡት እውቅና ለቀጣይ ስራ የሚያነሳሳ፣ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ እና የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንድንቀጥል እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ ስራዎችን እንድንጀምር የሚያበረታታ ነውም ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የክልሉ ፍርድ ቤቶች በውሳኔ ጥራት፣ በመዝገብ አፈጻጸም እና በሌሎች መለኪያዎች ካለፉት ዓመታት የተሻለ መፈጸማቸውን የተናገሩት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ለተመዘገበው አፈጻጸም ድርሻ ለነበራቸው በየደረጃው የሚገኙ የፍርድ ቤት አመራሮች፣ ዳኞችና ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በዘላቂነት ለማሻሻል በርካታ ስራዎች በዓመቱ መከናወናቸውን ያስታወቁት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ በመደበኛው ፍርድ ቤትና በሌሎች አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ጥራት ያለው እና ሕብረተሰቡ እምነት የሚጥልባቸው የዳኝነት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

ፍርድ ቤቶች ከአስፈጻሚው አካላት ጋር አንድ በሚያደርጓቸው የጋራ እና የትብብር ስራዎች ላይ ተቀራርቦ የመስራት ችግሮች ነበሩባቸው ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ለሕብረተሰቡ የጋራ ተጠቃሚነት፣ በፍትሕ እና በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት፣ ምቹ የስራ ከባቢዎችን ለመፍጠርና ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመገንባት ከአስፈጻሚው አካላት ጋር ተቋማዊ ነጻነታችንን ጠብቀን በትብብር መስራታችን እንቀጥላለን ብለው፣ የክልሉ መንግስት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች እንዲሳኩ ላደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በ 2019 በጀት ዓመት ልናሳካቸው የሚገቡ ትላልቅ እቅዶች አሉን ያሉት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ የተቋም እና የሰው ሀብት አቅም ግንባታ፣ ዲጂታላይዜሽን፣ የዳኝነት አገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍና፣ የብዝኀ ፍትሕ መስጫ አማራጮችን ማስፋት እና የቅንጅት ሥራዎች እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ ስራዎችን የምናከናውንበት ነው ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *