ASC Logo

Amhara Region

Supreme court

የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች የእውቅና እና የስራ ማስጀመሪያ መድረክ ለመታደም ባህርዳር ገቡ

የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች የእውቅና እና የስራ ማስጀመሪያ መድረክ ለመታደም ባህርዳር ገቡ

ባህርዳር ፣ ታህሳስ 20/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)


የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች የእውቅና እና የስራ ማስጀመሪያ መድረክ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የስራ ሀላፊዎች ፣ ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነገ ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም በልዩ ልዩ ዝግጅት በድምቀት ይካሄዳል።
ዝግጅቱን ለመታደም እንግዶች ከተለያዩ የሀገሪቱ እና የክልሉ አካባቢዎች ወደ ባህርዳር እየመጡ ሲሆን፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ሌሎች ሚኒስትር ዴኤታዎች በዛሬው እለት ባህርዳር ገብተዋል።
ሚኒስትሯን ጨምሮ የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እና ሌሎች እንግዶችም ባህርዳር ሲገቡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ የአማራ ክልል ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
እንግዶቹ ከጉባኤው አስቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ስራዎች ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን፣ በተለይም ሰው ተኮር በሆኑ ፕሮጀክቶች - ማለትም የዜጎችን እንግልት፣ ወጭ እና ጊዜ የሚቆጥቡ የርቀት ክርክሮች እና ኢ- ፋይሊንግ፣ ህፃን የያዙ ባለጉዳይ እናቶች እና አቅመ ደካሞች ማረፊያ እና ማጥቢያ ቦታዎች፣ የህፃናት ማቆያ፣ የሾፌሮች ማረፊያ እና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች በአይነታቸው የተለዩ እና ብዙ ቦታ ያልታዩ እንደሆኑ የገለጹት ሚኒስትሯ ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሰሩ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎችን አድንቀዋል።
የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና ለተደራሽ ፍትሕ በሚል መሪ ቃል ታህሳስ 21 እና 22/2018 ዓ.ም በሚካሄደው የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች የእውቅና እና የስራ ማስጀመሪያ መድረክ ፣በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጥናት የተለዩ 15 አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች እውቅና ተሰጧቸው ሙሉ በሙሉ እና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ወደ ስራ የሚገቡ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *