ባህር ዳር ፣ ህዳር 17/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመራቸውን ስር ነቀል የለውጥ ስራዎች ከዳር በማድረስ ጥራት ያለው፣ ተገማች፣ ተደራሽ እና በዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እና በሙያዊ ስነምግባር የላቀ ስብእና ባላቸው ዳኞች እና ሰራተኞች፣ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በላቀ ቁርጠኝነት በመስራት ላይ ነው።
የሁሉአቀፍ የለውጥና ማሻሻያ ስራችን ብቃት ያለው ዳኛ እና የሰው ሀይል ነው፤ ያለ ሰው የምንሰራው ስራ የለም የሚለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በሰው ሀይል አቅም ግንባታ ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ አካል የሆነ የእጩ ዳኞች የስራ ትውውቅ መድረክ ከህዳር 16 እስከ ህዳር 18/2018 ዓ.ም በመስጠት ላይ ነው።
በትላንትናው እለት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ልዩ ልዩ የትኩረት መስኮች የጀመረው መድረኩ፣ ዛሬም የስነምግባር ግንባታ እና የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ እንዲሁም የአማራ ክልል ዳኞች የስነ ምግባር እና የዲስፕሊን ደንቦች ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች በተደረገ ገላጻ ቀጥሎ ውሏል ።
የቀረበውን ገላጻ ተከትሎ ፣ በስነምግባር ግንባታ እና የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ ፣ በዳኞች የስነምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ እንዲሁም ከዳኞች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ የትምህርት እድሎች፣ ከዳኝነት ነጻነት እና ተጠያቂነት፣ እና ሌሎች ተያያዥነት የላቸው አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ በክቡር ፕሬዝዳንቱ እና በውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅራቢዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጦባቸዋል።
የዳኞች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቅም ገደብ የተቀመጠው ፍርድ ቤቶቻችን በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት ለማረጋገጥ፣ ዳኞቻችን አከራካሪ በሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ አስተያይት በመስጠት የዳኞችን ገለልተኛነት እና የፍርድ ቤቶችን ነጻነት ጥያቄ ውስጥ እንዳያስገቡ ለማድረግ ነው ያሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የሰው ሀይል አቅምን ለማሳደግም የሀገር ውስጥ እና የውጭ አጫጭር ስልጠናዎች እና የትምህርት እድሎች እየተመቻቹ መሆኑን ገልጸዋል።
ዳኞቻችን እርስ በእርስ እየተማማሩ የዳኝነት ጥራትን እንዲያረጋግጡ ለማድረግ የእውቀት አስተዳድር ስርዓት እየተዘረጋ ነው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ምርጥ ፍርዶችን በማሳተም፣ በተደጋጋሚ በሚቀርቡ እና አከራካሪ በሆኑ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ማጣቀሻ መጽሀፍትን በማዘጋጀት ለዳኞቹ የሚሰራጩ ይሆናል ብለዋል።
የዳኝነት ነጻነት ለዳኞች ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የተሰጠ መብት ነው ያሉት ክቡር ፕሬዘዳንቱ እጩ ዳኞቹ፣ ሁሉም መብቶች ከተጠያቂነት ጋር የተሰጡ መሆናቸውን በመረዳት የዳኝነት ሙያቸውን በላቀ የእውቀት እና የሙያ ስነምግባር ታግዘው እንዲያከናውኑ መልእክት አስተላልፈዋል።
የሙያ ትውውቅ መድረኩ ነገም ለሶስተኛ ቀን በተለያዩ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትኩረት መስኮች ቀጥሎ ይውላል።






