ASC Logo

Amhara Region

Supreme court

“የተጀመሩ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንጻ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት አለበት” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው -የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

“የተጀመሩ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንጻ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት አለበት” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው -የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

ባህር ዳር፣ ህዳር 18/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የህዝቡን እና የዳኝነት አካሉን ክብር የሚመጥኑ ምቹ የሥራ ቦታዎችን መፍጠር የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑ ታምኖበት በየደረጃው የሚገኙ የክልሉን ፍርድ ቤቶች የማስቻያ ቦታ እና የቢሮ ችግር ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም በግንባታ ላይ የሚገኙ የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ያሉበትን አፈጻጸም ደረጃ በተመለከተ ግንባታዎቹን የሚሰራው የዘመን ኮንስትራክሽን እና የፕሮጀክቶቹ አማካሪ የሆነው ልሕቀት የዲዛይን እና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ግምገማ የተደረገ ሲሆን ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርደ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው የተጀመሩ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ አሰሪው ፍርድ ቤት፣ ተቋራጩ እና አማካሪ ድርጅቱ አፈጻጸማቸውን በሚመለከት በየጊዜው በመገናኘት በጥልቀት መገምገም እና ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚገባ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በግምገማው የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንጻ ግንባታዎች በአመዛኙ ተጠናቀው ሊፍት የመግጠም ሥራ ብቻ የሚቀር ቢሆንም ፣ ሥራው በባለፈው በጀት ዓመት መጠናቀቅ ሲገባው እስካሁን ድረስ መቆየቱ ተገቢ አለመሆኑን፤ የባህር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የማዕከላዊ ጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም የአዊ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንጻ ግንባታም በተለያዩ ውጪያዊ እና ውስጣዊ ምክንያቶች የዘገዩ መሆናቸውን እና መዘግየቱን ሊያካክስ የሚያስችል ዕቅድ ታቅዶ በተያዘላቸው የማጠናቀቂያ ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉ ክቡር ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት የግንባታ ውል የተያዘለት የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አፈጻጸም ሲታይ በዝግጅት ምዕራፍ የተሰሩ ሥራዎች መልካም ቢሆኑም ወደ ዋናው ስራ በአፋጣኝ ሊገባ የሚገባ ስለመሆኑ ክቡር ፕሬዝደንት ገልጸዋል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመት ግንባታ ለማስጀመር የዲዛይን ሥራ የተሰራላቸው እና የሚሰራላቸው ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ያሉ መሆኑን የገለጹት ክቡር ፕሬዝደንቱ ፣ የባህር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንጻ ግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ በአካል በመገኘት ተመልክተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *