ASC Logo

Amhara Region

Supreme court

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ዳኝነት ሙያ ለሚቀላቀሉ እጩ ዳኞች የሙያ ትውውቅ ማካሄድ ጀመረ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ዳኝነት ሙያ ለሚቀላቀሉ እጩ ዳኞች የሙያ ትውውቅ ማካሄድ ጀመረ

ባህርዳር ፣ ህዳር 16/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል በርካታ የለውጥ ስራዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል።

ምቹ የስራ ከባቢ በመፍጠር፣ አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ፣ በተቋማዊ የለውጥ ስራዎች እና በሰው ሀይል አቅም ግንባታ ዘርፎች በልዩ ትኩረት እየሰራ ያለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ ከህግ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስር ሆኖ እንደገና በተደራጀው የአማራ ክልል የፍትሕና የህግ ኢኒስቲትዩት ላለፉት 8 ወራት በንድፈ ሀሳብና በተግባር ሙያ የቅድመ ስራ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው እጩ ዳኛ ለሆኑት የስራ ትውውቅ መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የስራ ትውውቅ መድረኩ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ፣ በቆይታቸው ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ፣ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የአምስት ዓመት እቅድ ፣ የዲጅታላይዜሽን ፕሮጀክት አፈጻጸም እና የቀጣይ እቅድ ፣ የፍርድ አጻጻፍ፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና የችሎት ስነስርዓት መመሪያዎች፣ የአማራ ክልል የዳኞች የስነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ እንዲሁም የችሎት መስተንግዶ ጭብጥ አያያዝ ማስረጃ አቀራርብ ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች እና ከፍተኛ ልምድ እና በተግባር የተፈተነ የዳኝነት አቅም ባላቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ገለጻዎችን እና ስልጠናዎችን ያገኛሉ።

የእጩ ዳኞችን የሙያ ትውውቅ መድረክ የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ወደ ፍርድ ቤቶቻችን በዳኝነት ሙያ የሚቀላቀሉት እጩ ዳኞች ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በየደረጃው ባሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የተገበራቸውን እና እየተገበራቸው ያሉ የለውጥ ስራዎችን መገንዘባቸው በላቀ ወኔ እና የህዝብ አገልጋይነት ስሜት የዳኝነት ሙያቸውን በመፈጸም፣ የተጣለባቸውን ተቋማዊና ሀገራዊ ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ፍርድ ቤቶቻችን የጀመሩትን ሁሉአቀፍ የለውጥ ስራ ተግባራዊ በማድረግ የፍርድ ጥራትን ማረጋገጥ ከሁሉም እጩ ዳኞች ይጠበቃል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ የስራ ላይ ትውውቅ ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል በላቀ እውቀት፣ ቁርጠኝነት እና የሙያ ስነምግባር ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በትውውቅ መድረኩ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የፍርድ አጻጻፍ፣ በፍርድ ቤቶች የእስካሁን የዲጅታላይዜሽን ትግበራ እና የቀጣይ እቅዶች እንዲሁም የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና የችሎት ስነስርዓት መመሪያዎች ላይ ለእጩ ዳኞቹ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች እና ዳኞች ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን፣ እጩ ዳኞቹ በቀረቡ ገለጻዎች ላይ ጥያቄዎችን እያነሱ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የፍርድ አጻጻፍ ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ በፍርድ አጻጻፍ ሂደት መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ፣ በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እና መፍትሄዎችን ካቀርቡት ክብርት ዳኛ ወይዘሮ በላይነሽ አቸነፍ ጋር እጩ ዳኞችን ያወያዩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተቀዳሚ አላማ ጥራት ያለው ፍርድ እና ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት መስጠት መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል እና ለማዘመን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በበርካታ የለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፈ መሆኑን ለእጩ ዳኞቹ ያስረዱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ለአሰራር ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት የሚያግዙ ህጎችን ማሻሻል፣ መመሪያዎችን መከለስ እና ማውጣት፣ የዳኝነት ነጻነትን ማረጋገጥ፣ ምቹ የስራ ከባቢን መፍጠር፣ ፍርድ ቤቶችን ተደራሽ ማድረግ ፣ የሰው ሀይል አቅምን መገንባት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የለውጥ እና የማሻሻያ ስራዎች ተፈጻሚነት የእያንዳንዱ እጩ ዳኛ ጥረት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል።

የትውውቅ መድረኩ ነገም ቀጥሎ የሚውል ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *