ባህርዳር፣ ህዳር 16/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመራቸውን የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች ከግብ ለማድረስ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በበጀት ዓመቱ በመደበኛነት ለማከናወን ከያዛቸው እቅዶች በተጨማሪ ፣ የተለያዩ የስራ ሂደቶች በመቶ ቀናት ውስጥ በልዩነት ለመተግበር የያዟቸውን እቅዶች አቅርበው ወደ ስራ እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን፣ የእቅዶችን አፈጻጸም፣ የተጠናቀቁትን እና በሂደት ያሉትን ክንውኖች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በተገኙበት ገምግሟል።
ክቡር ፕሬዝዳንቱ በጥቅምት፣ ህዳር እና ታህሳስ ወራቶች እንዲጠናቀቁ ለየስራ ክፍሎቹ ተለይተው የተሰጡት እና ሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ የስራ ክፍሎች በጋራ እንዲያከናውኗቸው የተለዩት የመጀመሪያው ዙር የ100 ቀናት እቅዶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቃቸው ለጀመርነው የለውጥ እና የማሻሻያ ስራ፣ የፍርድ ጥራት፣ ተደራሽነት እና የዳኞችና የሰራተኞች የስነ-ምግባር ቁጥጥር ትልቅ መሻሻል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ የዳኞች አስተዳደር ጽ/ቤት፣ የአይሲቲ ዳይሬክቶሬት፣ ሶስቱ የችሎት አስተባባሪዎች፣ የህዝብ ግንኙነት፣ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ጽ/ቤት እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የ100 ቀናት እቅድ አፈጻጸማቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የቀረቡ የእቅድ አፈጻጸሞች ያሉበትን ደረጃ የገመገሙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በ100 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቁ ከቀረቡት እቅዶች አብዛኞቹ በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቀሪ የእቅድ ስራዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ ለየስራ ክፍሎቹ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
