ባህርዳር ፣ የካቲት 12/2018 (የአማራ ክልል ጠ/ፍ/ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉ ህዝብ ለሕግ የበላይነት ያለውን እምነት እና ክብር የሚመጥን፣ እንደ ሀገር እና እንደ ክልል የተጀመሩና እየተመዘገቡ ያሉ የዳኝነት እና ለፍትህ ዘርፉ የለውጥ ሥራዎችን ታሳቢ ያደረገ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና መስሪያ ቤት፣ ድንበር ዘለለ እና ሀገር በቀል የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ተከትለው የሚመጡ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ አለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት የልህቀት ማዕከል (International Arbitration and Mediation Excellence Center) እና የህግ የበላይነት እና የሰላም ማዕከል (Rule of law and Peace Center) የያዘ እና ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት እና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ የተማከለ የዳኝነት ኮምፕሌክስ ለማስገንባት ዝግጅቱን አጠናቋል።
የሚገነባው ኮምፕሌክስ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ በግንባታ ጥራት እና በሚሟሉለት የዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች፣ ከክልሉ አልፎ ለሀገር እና ለአፍሪካ የዳኝነት ተቋማት አርአያነት የሚኖረው እና ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚኖረው ይሆናል።
በውል ስምምነቱ ወቅት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የማማከር ሀላፊነቱን ለኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲሰጥ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እድሳት እና ማስፋፊያ ግንባታ በጥራት እና በአጭር ጊዜ በሀላፊነት ስሜት መከናወኑን፣ ሌሎች ክልል እና ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በጊዜ ማጠናቀቁን ታሳቢ በማድረግ ነው ያሉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የማማከር ስራውን ለኮርፖሬሽኑ በመስጠታቸው ደስተኛ መሆናቸውን እና ኮርፖሬሽኑም በጥራትና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንደሚያጠናቅቀው ሙሉ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽናቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ታንዛኒያ እና ናይጀሪያን ጨምሮ ላለፉት 60 ዓመታት በተለያዪ አገራት በማማከር፣ በዲዛይን እና በግንባታ እና ውል በማስተዳደር ስራ የዳበረ ልምድ እንዳለው የጠቀሱት የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ም/ዋ/ስራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር ካሳሁን በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰጣቸው ሀላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱን በጥራት እና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ የተሰጣቸውን የማማከር ሃላፊነት በአግባቡ እንወጣለን ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚያስገነባው የተማከለ የዳኝነት ኮምፕሌክስ ግንባታው በ 15 ሄክታር ላይ ያርፋል። አጠቃላይ የግሪነሪና ላንድስኬፕ ስራውን ጨምሮ 20 ሄክታር ላይ የሚሰራ ሲሆን፣ ግንባታው በ 3 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል።
English
