ባህርዳር ፣ መጋቢት 06/2018 (አማራ ክልል ጠ/ፍ/ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል ይዞት የተነሳውን ርዕይ ከግብ ለማድረስ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት እየሰራ ይገኛል።
በየደረጃው የሚተገበሩ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እቅዶች እውን ለማድረግ ከመደበኛው የተቋሙ ዓመታዊ እቅድ በተጨማሪ በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ የመቶ ቀናት እቅዶችን በማዘጋጀት ሥራዎችን እያከናወነ ያለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ በመጀመሪያው መቶ ቀናት የተከናወኑ ዋና ዋና አፈጻጸሞችን መነሻ በማድረግ በተዘጋጁ የቀጣዮቹ መቶ ቀናት እቅዶች ላይ ተወያይቷል።
ከመስከረም 21 እስከ ታህሳስ 30/ 2018 ዓ.ም በቆየው የመጀመሪያው የ100 ቀናት እቅድ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የተማከለ የዳኝነት ኮምፕሌክስ ግንባታ ለማስጀመር፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን በክልሉ የተለያዩ ቀበሌዎች ስራ ለማስጀመር፣ በክልሉ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ለጀመረዉ ስራ ግብዓት የተገኘበት አለምአቀፍ ጉባኤ ለማካሄድ፣ የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዘመናዊ አዳኝነት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለማድረግ በዲጅታላይዜሽን መሰረተ ልማት እና አገልግሎት አሰጣጥ የተቀመጡ እቅዶችን በማሳካት ረገድ፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማረጋገጥና በሌሎች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትኩረት መስኮች ላይ በርካታ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን የገመገመው የጠቅላይ ፍ/ቤት የትራንስፎርሜሽን ቡድኑ፣ ከመጋቢት 05 እስከ ሰኔ 15/2018 ዓ.ም በሚከናወኑ የቀጣይ መቶ ቀናት እቅዶች ላይ በጥልቀት ተወያይቷል።
ውይይቱን የመሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በመጀመሪያው መቶ ቀናት የታቀዱ እና የተከናወኑ ሥራዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የክልሉን ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ፣ ተገማች፣ ተደራሽ እና ወጭ ቆጣቢ በማድረግ የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል ለያዘው ርዕይ ተፈጻሚነት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው ፤ በተለይም የተጀመረዉ የዲጅታላይዝሽን ሥራ የዜጎቻችንን እንግልት ፣ወጭ እና ጊዜ ትርጉም ባለዉ ሁኔታ የቀነሰ በመሆኑ ሁሉም የተቋሙ ባልደረቦች ሊኮሩበት የሚገባ መሆኑን አስታውሰው እና ለዚህ ስኬት ለሰሩ ሁሉም አካላት ምስጋና አቅርበዉ ፣ የቀጣዮቹ መቶ ቀናት እቅዶች ትኩረትም የተቋሙን አላማ እና ርዕይ ለማሳካት በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተማከለ የዳኝነት ኮምፕሌክስ ግንባታ የማስጀመር ሂደት፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን በተሟላ ሁኔታ መደገፍ ፣ የዘመናዊ እና ዲጅታል ፍርድ ቤቶች በክልሉ እውን መሆን፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን በመሰረታዊነት ማሻሻል፣ የዳኞችን፣ የሰራተኞችን አቅም ማጎልበት፣ በሥነ-ምግባር ረገድ የሚነሱ ጉዳዮችን ማረምና ዘላቂ መፍትሄ እየሰጡ መሄድ፣ የተቋሙን የመዋቅር እና የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች ማጠናቀቅ ዋናዎቹ የተቋማችን የትኩረት መስኮች ናቸዉ ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ በየክፍሎቹ የተዘጋጁት የ 2ኛው ዙር መቶ ቀናት እቅዶች ዉስጥ የተካተቱ ተግባራትም ይሄንን ታሳቢ አድርገው የታቀዱ መሆናቸዉ መረጋገጥ እና መተግበር አለባቸው ብለዋል።
የተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች ያቀረቧቸው እቅዶች ለተቋሙ ርዕይ መሳካት የጎላ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹት የትራንስፎርሜሽን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው፣ እቅዶቹ በልዩ ትኩረት ሊተገበሩ እንደሚገባ አንስተው፣ ሁሉም የስራ ሂደቶች በጋራ እና በተናጠል ስራዎችን በማከናወን እቅዶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በትኩረት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸዉን አረጋግጠዋል፡፡