ASC Logo

Amhara Region

Supreme court

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራር እና ሰራተኞች የክልሉን ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ገመገሙ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራር እና ሰራተኞች የክልሉን ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ገመገሙ

ባህርዳር ፣ ጥቅምት 26/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

በሁሉአቀፍ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፣ በ 2017 በጀት ዓመት በሰው ሀይል አቅም ግንባታ፤ ምቹ የስራ ከባቢ በመፍጠር ፣ ለዳኝነት ነጻነት መረጋገጥ ፣ የባህል ፍርድ ቤቶችን እውቅና ለመስጠት ፣ ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የመሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት እና በሌሎች ተቋማዊ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች የሚታዩ ውጤቶችን ማስመዝገቡ ይታወቃል።

በ 2017 በጀት ዓመት በተከናወኑ ሁሉ አቀፍ የለውጥ ስራዎች መነሻነት፣ በዓመቱ በድክመት የተለዩ አፈጻጸሞችን በመለየት በተሻለ መነቃቃት እና የአገልጋይነት ስሜት የ 2018 በጀት ዓመት የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን የጀመረው ፍርድ ቤቱ ፣ በዛሬው እለት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያከናወናቸውን ስራዎች ገምግሟል።

የሩብ ዓመቱ የስራ አፈጻጸም ግምገማ የተካሄደው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች ፣ ዳኞች እና ከየሄደቱ የተወጣጡ ሰራተኞች በተገኙበት ሲሆን ፣ በዓመቱ ለመስራት ከታቀደው አንጻር ፣  በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ የስራ አፈጻጸሞች  ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፣ የበጀት ዓመቱን የጀመርነው በመላው የክልላችን ፍርድ ቤቶች ለሚገለገሉ ባለጉዳዮች ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ፣ አመኔታን ያተረፈ ፣ ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የጋራ ርዕይ በመሰነቅ እና በላቀ ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።

የሩብ ዓመቱን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት  ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ በበኩላቸው ፣ የክልሉ ፍርድ ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት የነበራቸው አፈጻጸም በብዙ መለኪያዎች ሲመዘን በፍርድ ቤቶች ታሪክ ከፍተኛ አፈጻጸም የታየበት መሆኑን ገልጸው ፣ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸመም ፣ ፍርድ ቤቶቻችን የላቀ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችላቸው መልካም ቁመና ላይ እንደሚገኙ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከመስከረም 20 እስከ መስከረም 29/2018 ዓ.ም የተካሄደው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ጉባኤ፣  መላው የክልሉ ፍርድ ቤቶች ተናባቢ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስቻለ መሆኑን ፣ በወቅቱ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ የቀረቡት ስልጠናዎች ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ርዕይ የሁሉም ፍርድ ቤቶች ፣ ዳኞች እና ሰራተኞች የጋራ ርዕይ እንዲሆን ለማድረግ ፣ የጋራ  ርዕይ ለጠንካራ የዳኝነት አገልግሎት በሚል የተካሄደው ጥልቅ ውይይት ፍሬ እያፈራ መሆኑን በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ አፈጻጸሞች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በሩብ ዓመቱ በዝግጅት እና በተግባር ምእራፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ ተሳታፊዎች ሀሳብና አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ፣ ከበጀት ዓመቱ የሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተው በፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንቶች ምላሽና መብራሪያ ተሰጦባቸዋል።

ተሳታፊዎችን ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን ጋር ያውያዩት ፣  የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ በ2017 በጀት ዓመት ስኬታችን ሳንዘናጋ፣ በላቀ ቁርጠኝነት የዳኝነት አገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብ ፍላጎት ማርካት በሚችል ቁመና ላይ ልንገኝ ይገባል ብለው ፣ የክልሉን ፍርድ ቤቶች የላቀ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለማድረግ በ2017 በጀት ዓመት የተከናወኑ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር እና  አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር የ2018 በጀት ዓመት  እቅዳችንን በላቀ አፈጻጸም ማሳካት ይኖርብናል ብለዋል።

የባህል ፍርድ ቤቶችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እውቅና መስጠት እና ስራ ማስጀመር ፣ የዳኞች የግልግል ዳኝነት ማሰልጠኛ ማዕከልን ጨምሮ በውስጡ በርካታ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ ህንጻ ግንባታ ማስጀመር ፣ ፍርድ ቤቶቻችን የጀመሩትን የለውጥ ሂደት ይበልጥ ለማስቀጠል በርካታ ግብዓት የሚገኝበት አለምአቀፍ ጉባኤ ማካሄድ ፣ የፍርድ ቤቶቻችን ዋነኛ ስራ ለሆነው የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ፣ ቅልጥፍና እና ታማኝነት ያረጋገጥ አገልግሎት መስጠት ፣ በዳኞቻችን እና በመላው ሰራተኞቻችን የስነ ምግባር ሁኔታ ላይ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት ፣  የ2018 በጀት ዓመት ዋነኛ የትኩረት መስኮቻችን ናቸው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ ለሀሳቦቹ ተፈጻሚነት በየደረጃው የሚገኙ የፍርድ ቤቶች አመራሮች ፣ ዳኞች ፣  የጉባኤ ተሿሚዎችና ሰራተኞች በላቀ የአገልጋይነት ስሜት ስራቸውን እንዲያከናዉኑ አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *