ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የጥብቅና አገልግሎትን ጨምሮ አጠቃላይ የሕግ አገልግሎት ዘርፍ መሻሻል  ፍ/ቤቶች ጥራት ያለዉ የዳኝነት አገልግሎት ወይም ትክክለኛ ፍትህ እንዲሰጡ በማገዝ ረገድ ወሳኝ ድርሻ አለዉ፡፡ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው – የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

“የጥብቅና አገልግሎትን ጨምሮ አጠቃላይ የሕግ አገልግሎት ዘርፍ መሻሻል  ፍ/ቤቶች ጥራት ያለዉ የዳኝነት አገልግሎት ወይም ትክክለኛ ፍትህ እንዲሰጡ በማገዝ ረገድ ወሳኝ ድርሻ አለዉ፡፡ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው – የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

ባህርዳር ፣ ጥቅምት 30/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በሚያደርገው ሁሉ አቀፍ የለውጥ ሂደት ውስጥ ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይቶች እያካደ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በዳኝነት  ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ለማስተካከል ፣ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን በዘላቂነት ማስቀጠል በሚቻልባቸው አግባቦች እና በዳኝነት እና በፍትሕ ስርዓቱ መሻሻል ላይ የበኩላቸውን ድርሻ የሚወጡ ባለድርሻ አካላት ማድረግ ባለባቸው አስተዋጽኦ ከክልሉ ጠበቆች ጋር የመጀመሪያዉን ዙር ውይይት አካሂዷል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የክልሉን የዳኝነት ሥርዓት በመሰረታዊነት ለማሻሻል ከያዛቸው እና በትግበራ ላይ ካሉ አሰራሮች አንዱ የሆነው የዲጅታላይዜሽን ትግበራ ለጠበቆች የቀረበ ሲሆን ፣ ጠበቆች ዘመኑ የሚጠይቃቸው የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ዘዴዎች ላይ እውቀቱ ኖሯቸው ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎች ጋር አብረው መራመድ እንዳለባቸው ተገልጿል።

በተዋረድ የሚተገበርው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዲጅታላይዜሽን ስራ ጅማሮ ፣ አስፈላጊነት ፣ አሁናዊ ሁኔታና እና የወደፊት እቅድ በዝርዝር ቀርቦላቸዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የተከናወኑ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ፣ ምቹ የስራ ከባቢ ለመፍጠር የተከናወኑ አዳዲስ ህንጻ ግንባታዎችን ፣ የነባር ህንጻ እድሳት እና  የዜጎች መሰረታዊ መብት የሆነውን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት ያከበረ የችሎት አገልግሎት ለመስጠት የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ጠበቆቹ ፣ በቀረበው የለውጥ እና የማሻሻያ ስራ ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግቢ ተዘዋውረው ባዩት የተቋም እና የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም  የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል  የተጀመሩ መልካም ጅምሮችን ማስቀጠል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች እና ከእያንዳንዱ ጠበቃ ምን ይጠበቃል በሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ  ሀሳብና አስተያይታቸውን ሰጠዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትልቅ ተቋም ነው ፤ በዳኝነት እና በህግ የበላይነት የሚያምን ማህበረሰብ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ ተቋም ነው ያሉት የውይይቱ ተሳታፊ ጠበቆች ፣ የተጣለበትን ህግን የማስከበር ከፍተኛ ሀላፊነት እንዲሁም የክልሉን ማህበረሰብ በሚመጥን ልክ ሆኖ እንዲገኝ እየተሰሩ ባሉ  የማሻሻያ እና የለውጥ ስራዎች ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

ለባለጉዳዮች፣ ለዳኞች ፣ ለሠራተኞች እና ለጠበቆች ምቾት የሚሰጥ ፣ የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር የዳኝነት ተቋም እየተፈጠረ ነው ያሉት ጠበቆቹ ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ የተጀመሩ ስራዎች በሌሎች የዞን እና የወረዳ ፍርድ ቤቶች ሊተገበሩ እንደሚገባ፣ እንዲሁም የዳኝነት እና የፍትሕ ስራ የአንድ ተቋም ስራ ብቻ ባለመሆኑ ሌሎች የፍትሕ ተቋማትም በተመሳሳይ ቁመና ላይ እንዲገኙ በትብብር መስራት እና አብረው መራመድ እንዲችሉ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋምን በዚህ ደረጃ ለመቀየር ደፋር ፣ ቆራጥ እና ውሳኔ ሰጪ የሆነ አመራር ያስፈልጋል ያሉት ጠበቆቹ ፣ የክልሉን ፍርድ ቤቶች ማህበረሰቡ የሚተማመንባቸው ምቹ ፣ ዘመናዊ፣ ሙያዊ ስነምግባርን የተላበሱ እና ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ  ለማድረግ በተከናወኑ  እና እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ ጉልህ የመሪነት ሀላፊነት ያላቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ፕሬዝዳንት፣ አመራሮችን እንዲሁም  የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ስራ በሀሳብ፣ በገንዘብ እና በአይነት እያገዙ ያሉትን በሙሉ አመስግነዋል።

የተጀመሩ ሥራዎችን ማስቀጠል የሚችሉ ዳኞች፣ አመራሮችና ባለሙያዎችን ማፍራት ያስፈልጋል ያሉት ጠበቆቹ ፣ ከዳኝነት ጥራት እና ከውሳኔ ተፈጻሚነት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከተሳታፊ ጠበቆች ለቀረቡ አስተያይቶች እና ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ በሙያዊ ስነ-ምግባር እና በእውቀት የላቁ ዳኞችን ለማፍራት በሰው ሀብታችን ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

ምቹ የሥራ ቦታዎች  እና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ያለ ሰው ምንም ናቸው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ ለስራ ቦታዎች እና ለቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ከሰጠነው ትኩረት ጋር በትይዩ የሚሄድ ሰፊ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ ስራ ላይ ነን ብለዋል።

የውጭ ሀገር የትምህርት እድሎችን ጨምሮ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች ለዳኞች ፣ ለጉባኤ ተሿሚዎችና ለአስተዳደር ሰራተኞች በመሰጠት ላይ ናቸው ብለዋል። የአማራ ክልል ፍትህና የሕግ ኢንስቲትዩት ለጠቅላይ ፍ/ቤት ተጠሪ ሆኖ በስልጠና እና ምርምር የልህቀት ማዕከል እዲሆን ታስቦ እየተሰራ ሲሆን የቅድመ ሥራና የሥራ ላይ ስልጠናዎች ታስቦባቸዉ እንዲሰጡ እየተደረገ ነዉ ፤

ዳኞች አቅማቸውን የሚፈጥሩበት ፣አንዱ ከሌላው የሚማርበት የጋራ የውይይት መድረክ  በየ 15 ቀኑ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነን ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣  ለዳኞች እና ለጠበቆች እንደ ማጣቀሻነት የሚያገለግሉ ትኩረታቸውን በፍርድ ቤቶቻችን በብዛት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ያደረጉ ማጣቀሻ ጽሁፎች ይዘጋጃሉ ብለዋል።

ጠበቆች በዳኝነት እና በፍትሕ ስርዓቱ  መሻሻል  ላይ ያላችሁ  ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ ፍርድ ቤቶቻችን ትክክለኛ ፍርድ እና ጥራት ያለው ውሳኔ ለመስጠት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ሀላፊነታችሁን በአግባቡ  ልትወጡ ይገባል ብለዋል። ከዳኝነት ሥነ-ምግባር አንጻር የሚነሱ ችግሮችም ከጠበቆች ሥነ-ምግባር የተሳሰሩ በመሆኑ ጠበቆች ከመቼዉም ጊዜ በላይ ለሙያ ሥነ-ምግባር ተገዥ እንዲሆኑ እና የእርስ በእርስ ቁጥጥሩን በማጠናከር የሙያዉን ክብር ማስጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ክቡር ፕሬዘዳንቱ ጠበቆችን ጨምሮ በዐቃቤ ሕግ፣ በተከላካይ ጠበቆች፣ በነገረ ፈጆች  እና በሌሎች አካላት የሚሰጠዉ የሕግ አገልግሎት (Legal Service) መሻሻል ፍ/ቤቶች ጥራት ያለዉ የዳኝነት አገልግሎት ወይም ትክክለኛ ፍትህ እንዲሰጡ በማገዝ ረገድ ወሳኝ ድርሻ ያለዉ በመሆኑ ለዚህ በቂ ስትራቴጅዎች ተቀርጸዉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዉ አዲሱን የጠበቆች አዋጅ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አንዱ ለዘረርፉ መሻሻል ወሳኝ ድርሻ ያለዉ ነዉ ብለዋል፡፡

በሚታዩ የሥነ- ምግባር ጥሰቶች ላይ ጥቆማዎችን በመስጠት ፣ የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት ለማሻሻል የምናደርጋቸውን የጥናት ሥራዎች በማገዝ እና የውሳኔ ጥራት ችግር የሚስተዋልባቸውን የአቅም ችግሮች  በመለየቱ ሂደት እገዛችሁን እንፈልጋለን ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ እንደ ክልል ነጻና ገለልተኛ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋም ለመገንባት በምናደርገው ጥረት ውስጥ ለሀቅ እና ለእውነት በመቆም አብራችሁን እንድትሰሩ አደራ እላለሁ ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *