ባህርዳር ፣ ጥቅምት 28/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)
የትብብር መድረኩ በክልሉ መንግስት የተዘጋጀውን የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታን ለማስተግበር የተዘጋጀውንና ከ2018 ዓ.ም እስከ 2022 ዓ.ም የትግበራ ጊዜ የተቀመጠለትን የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ የ 5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በተመለከተ ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም ውይይት መጀመሩ ይታወቃል።
በዚህም የመድረኩ አባል ተቋማት ፣ በትናንትናው እና በዛሬው ውሏቸው የየተቋማቱ ስትራቴጂክ ዕቅዶች እና አሰራራቸውን ለማሻሻል ያግዙናል ያሏቸውን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚተገባሩ የአሰራር ማዕቀፎች እንዲሁም አንዱ ተቋም ከሌላኛው ተቋም ሊቀስማቸው የሚገቡ ተሞክሮዎችን በዝርዝር አቅርበው ሰፊ እና ውጤታማ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት ከየካቲት 07 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆኖ እንደገና ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ለማሻሻል የሚያስችል ዕቅድ አቅዶ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን፣ በዚህም ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በሚያሻሽሉ እና የመፈጸም አቅምን በሚያጎለብቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሥልጠናዎችን ከመስጠት ጎን ለጎን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንዲሁም የክልሉ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት የመረጃ ማዕከል በመሆን እንዲያገለግል የተጣለበትን ከፍ ያለ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በመሰረተ ልማት ሥርጋታ እና በሰው ሐብት ልማት ሥራዎች በሚመለከት ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጋራ እና የተናጠል የ 5 ዓመት እቅዱን ለትብብር መድረኩ ያቀረበ ሲሆን ፣ ለእቅዱ መሳካት የሚያግዙ እና የተጀመሩ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች ለተሳታፊዎች አቅርቧል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያከናወናቸውን ሥር ነቀል የለውጥ ሥራዎች፣ በተለይም ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር እና የዳኝነት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተሰሩ ሥራዎች ለትብብር መድረኩ አባል ተቋማትም ሆነ ለሌሎች ተቋማት ከፍተኛ ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ፣ የለውጥ ሥራዎቹ በበታች ፍርድ ቤቶችም እንዲተገበሩ በማድረግ የባለጉዳዮችን እርካታ ያረጋገጡ እና በኅብረተሰቡ አመኔታ ያተረፉ ፍርድ ቤቶችን መገንባት የሚገባ ስለመሆኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ሥራው በሌሎቹ የትብብር መድረኩ አባል ተቋማትም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እና የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን በሚመለከት በቴክኖሎጂ አሰራር ትስስር ሊፈጠር የሚገባ ስለመሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ሠብዓዊ መብቶችን ማሳዎቅ፣ ማስከበር እና ማክበር፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፍ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተገማች፣ ወጥነት እና ጥራት ያለው የፍትሕ አገልግሎትን በማረጋገጥ የህዝብ አመኔታ እና ቅቡልነት ያላቸው የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን በመገንባት በክልሉ ውጤታማ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓትን ማስፈን የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት አመራሮች እና ባለሙያዎች ከፍ ያለ ሥነ-ምግባር ተላብሰው በቁርጠኝነት የፍትሕ አገልግሎት መስጠት የሚገባቸው ስለመሆኑ እና በየተቋማቱ የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ችግሮችን በጥናት በመለየት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የሚያስፈልግ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡










