ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በክልሉ የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፍ የ 5 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

በክልሉ የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፍ የ 5 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

ባህርዳር ፣ ጥቅምት 27/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትህ አካላት የትብብር መድረክ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ፣ በክልሉ የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፍ የ 5 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።

የክልሉን የዳኝነት እና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ በጋራ ቅንጅት ለማሻሻል ፣ ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ተቋማዊ ነጻነታቸውን ጠብቀው በትብብር ለመስራት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፍትህ ቢሮ፣ ፖሊስ ዋና መምሪያ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፣ የክልሉን የዳኝነት እና የፍትህ አካላት ትብብር መድረክ መስርተው በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 297/2017 የህግ መሰረት እንዲኖረው ተደርጎ እና በአዋጁ አንቀጽ 5(7) መሰረት የራሱ ጽ/ቤት ተቋቁሞለት፣ የማስተግበሪያ ቻርተር በመፈራረም በተጠናከረ መልኩ ወደ ስራ የገባው የትብብር መድረኩ ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰብሳቢነት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ከገባበት መስከረም 23/2017 ጀምሮ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በክልሉ የዳኝነት እና የፍትህ ስርዓት መሻሻል ውስጥ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ በመወጣት ላይ ይገኛል።

ከክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ የተቀዳ የራሱን የ 5 ዓመት የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፍ የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ የገባው የትብብር መድረኩ ፣ እቅዱን ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን የዳኝነት እና የፍትህ ስርዓት በመሰረታዊነት ማሻሻል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክሯል።

የምክክር መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ የዳኝነት እና የፍትህ አካሉ በልማት እና የመልካም አስተዳደር ሂደት ውስጥ ያለውን ጉልህ ድርሻ ባለመረዳት ፣በሀገር እና በክልል ደረጃ በሚካሄዱ የዘላቂ ልማት እቅዶች ውስጥ ዘርፉን እንደ አንድ ተዋናይ ያለማየት አዝማሚያዎች እንደነበሩ አንስተው፣ አሁን ላይ ክልሉ ባዘጋጀው የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ ውስጥ ፣ የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፉ በልዩ ትኩረት መካተቱ የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ እና የፍትህ ስርዓት ለማሻሻል በምናደርገው ጥረት ውስጥ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርልን ነው ብለዋል።

የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፉ በታሳቢነት የሚቀመጡ ነበሩ ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የሰላም መስፈን፣ የፍትህ መስፈን ፣ እንዲሁም የዳኝነት እና የፍትህ አካላት ነጻና ገለልተኛ ሆነው መጠናከራቸው ፣ በሀገር ሰላምና መረጋጋት ፣ በማጣኔ ሀብት እና ጤናማ ማህበራዊ መስተጋብር ላይ የሚኖራቸውን የጎላ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘርፎቹ መጠናከር እየተደረገ ያለውን ጥረት፣ ነጻና ገለልተኛ ሆነው ጠንካራ ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግ የተሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።

በእለቱ የዘርፉ የ5 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ በዝርዝር ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ፣ የዳኝነት እና የፍትህ አካላት የትብብር መድረክ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

የህግ የበላይነት መስፈን፣ የተደራጀ የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ማካሄድ፣ ዜጎች የሚተማመኑበት ነጻና ገለልተኛ የዳኝነት ስርዓት መስፈን፣ ታራሚን የሚያንጽ እና የወንጀል ድግግሞሽን የሚያስቀር ፣ ሰብዓዊ መብትን አክብሮ የሚያስከብር የማረሚያ ቤት ተቋም መኖሩ ፣ ዜግች፣ አልሚዎች እና ባለሀብቶች በነጻነት ሀብት እና ንብረት ማፍራት እንዲችሉ ያስችላቸዋል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ ይሄም ለጠንካራ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ዝርጋታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

አለመግባባቶች መፈታት ያለባቸው በዳኝነት እና በፍትህ አካላት ነው ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ይሄ እንዲሆን ደግሞ ዘርፉ ለህግ የበላይነት መስፈን እና ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ያለውን አስተዋጽኦ መረዳት ጠንካራ ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቆም ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የ 5 ዓመቱ የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፍ የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት እቅድ ፣ እንደ ተቋም በዳኝነት እና በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት አገልግሎት ፈላጊው የሚተማመንባቸው ፣ አሰራራቸውን ያዘመኑ፣ ነጻ፣ ገለልተኛ ፣ ተገማች ፣ ቀልጣፋ እና ወጭ ቆጣቢ የዳኝነት እና የፍትህ አገልግሎት እንድንሰጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን እንድንተገብር የትላንት ችግራችንን የለየ፣ የነገ መፍትሄዎችን ያመላከተ ነው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ የዳኝነት እና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጡ በአንዱ ተጀምሮ በሌላው የሚያልቅ እና የአንዱ ጥንካሬ ለሌላው ጥንካሬ በመሆኑ ፣ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተቋማዊ ነጻነታቸውን ጠብቀው በጋራ በመስራት ፣ ለእቅዱ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ጥረት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የጋራ ውይይቱ ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን ፣ የትብብር መድረኩ አባላት የተናጠል የ 5 ዓመት ተቋማዊ ስትራቴጂክ እቅዶቻቸውን አቅርበው ውይይት የሚካሄድባቸው እና አንዱ ከሌላው ልምድና ተሞክሮ የሚወስድበት ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *