ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ዳኞች አከራካሪ በሆኑ የህግ ጉዳዮች ላይ የጋራ መረዳት እንዲኖራቸው የሚያግዛቸውን የመጀመሪያውን የውይይት መድረክ አካሄዱ

የአማራ ክልል ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ዳኞች አከራካሪ በሆኑ የህግ ጉዳዮች ላይ የጋራ መረዳት እንዲኖራቸው የሚያግዛቸውን የመጀመሪያውን የውይይት መድረክ አካሄዱ

ባህር ዳር ፣ ህዳር 1/2018 ( አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ 2018 በጀት ዓመት በልዩ ትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ የውሳኔ ጥራት ማሳደግ ነው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ በተዋረድ የሚገኙ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን አቅም ለማጎልበት ከያዛቸው እቅዶች መካከል አንዱ በዳኞች መካከል የሚካሄድ የጋራ ውይይት ሲሆን ፣ አላማውም ዳኞች አከራካሪ በሆኑ የህግ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ተገማች እና ጥራት ያለው ውሳኔ ሰጪነትን ማሳደግ ነው።

ውይይቱ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ደኞች የተጀመረ ሲሆን፣ በቀጣይ በሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ እና በመደበኛነት የሚቀጥል የአቅም ማጎልበቻ ሙያዊ የውይይት መድረክ መሆኑን፣  የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው  ተናግረዋል።

የዳኞች የአቅም ግንባታ ጠንካራ ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት ከያዝናቸው የተቋም ግንባታ ምሰሶዎች አንዱ ነው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ የዳኞችን በጥራት የመወሰን አቅም ለማጎልበት ከያዝናቸው የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች በተጨማሪ፣ በክልሉ ፍርድ ቤቶች በብዛት በሚቀርቡ እና አከራካሪ በሆኑ ጉዳኞች ላይ ዳኞቻችን በስራ ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እያመጡ እንዲወያዩ እና አንዱ ከሌላው እንዲማር በማድረግ ወጥነት ያለው አረዳድ እና ተገማችነት ያለው ውሳኔ እንዲሰጡ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረው የውይይት መድረክ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

ከውይይት መድረኩ በተጨማሪ ፣ ዳኞች አለምአቀፍ፣ ሀገር አቀፍና ክልላዊ የሆኑ አዋጆችን፣ መመሪያዎችን ፣ ውሳኔዎችን እንዲሁም ከዳኝነት ስራቸው ጋር ግንኙነት ያላቸውን የህግ መጻህፍት የሚያገኙበት  የእውቀት አስተዳደር ቋት የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የጋራ መረዳት እንዲኖራቸው የሚያግዙ ማጣቀሻ መጻህፍት ዝግጅትም  እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች በተካሄደው የጋራ የውይይት መድረክ ፣  በክልሉ ፍርድ ቤቶች በብዛት ከሚቀርቡት ክርክሮች አንዱ በሆነው በገጠር መሬት ህግ አተረጓጉም ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን ፣ የውይይቱ ተሳታፊ ዳኞች በጉዳዩ ላይ ከችሎት ገጠመኞቻቸው ጋር የተያያዙ ሀሳቦችን እያነሱ ተወያይተዋል።

የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ፣ ክብርት ዳኛ ሳባ አበረ ሲሆኑ ፣ በገጠር መሬት ህግ አተረጓጉም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በሚል ርዕስ ፣ የተለያዩ የገጠር መሬት አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች  ፣ የአዋጆችን ይዘት እና ተፈጻሚነት ፣ አዋጆችን በግልጽ ካለመረዳት  የሚስተዋሉ የውሳኔ ችግሮችን በዝርዝር አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በቀረበው የውይይት መነሻ ጽሁፍ ላይ በስራ ላይ የሚገጥማቸውን የአፈጻጸም ችግር እያነሱ የተወያዩት ዳኞቹ፣ የውይይቱ መጀመር አከራካሪ በሆኑ እና አዳዲስ አዋጆች ላይ በቂ መረጃ ኖሯቸው በጥራት እንዲወስኑ ትምህርት የሚያገኙበት እና ለተጨማሪ ንባብ የሚነሳሱበት መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ በተከታታይነት እና በቋሚነት ሰፊ ጊዜ ተመድቦለት ሊካሄድ ይገባል ያሉት ዳኞቹ ፣ ከዳኞች በተጨማሪም አዋጆችን ያረቀቁ፣ ተመራማሪዎች እና በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ልምድና እውቀቱ ያላቸው ባለሙያዎች እየተጋበዙ ማብራሪያ እንዲሰጡ አስተያይታቸውን ሰጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *