ባሕር ዳር፣ መስከረም 29/2019 ዓ.ም (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረትን ጨምሮ የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በዛሬው እለት ባሕር ዳር ከተማ ገብተዋል።
ከጉባኤው አንድ ቀን አስቀድመው ባሕር ዳር የተገኙት ፕሬዘዳንቶቹ፣ የዳኝነት ተደራሽን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ በቆየው የክልሉ ፍርድ ቤት ዳኞች 2ኛ ዓመታዊ ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
በጉባኤው የመዝጊያ ስነስርዓት የተገኙት ፕሬዝደንቶቹ፣ በባህርዳር አለምአቀፍ ስታዲየም የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ አካሂደዋል።
የእግር ኳስ ጨዋታው የፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቶች ከተቋማዊ ኃላፊነታቸው ባሻገር እንዲገናኙ እድል የሰጣቸው ሲሆን፣ ስፖርት ጓደኝነትን፣ የቡድን ሥራን፣ የጋራ መግባባትን እና ሙያዊ አንድነትን በማሳደግ ረገድ ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳይ ነበር።
በነገው እለት ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎችን ጉባኤ በጋራ የሚያካሂዱት ፕሬዝደንቶቹ፣ ጉባኤው በሀገሪቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች መካከል ትብብርን ለማጠናከር እና በሀገሪቱ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት ላይ በመምከር የሚበጀውን ለመወሰን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው።










