ባሕርዳር፣ ጥቅምት 01/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ልዩ ጉባኤ መስከረም 30/2019 ዓ.ም በባሕርዳር ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በጋራ የሚተገብሩትን የትራንስፎርሜሽን ማእቀፍ ተወያይቶ ያጸደቀው ልዩ ጉባኤው፣ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ጋዛሊ አባሲማል የሽኝት መረሃግብር አካሂዷል።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ማእቀፍ ከሃሳብነት ተነስቶ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ከፌደራል እና ከሌሎች ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶች ጋር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ያለው ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ፣ ክቡር አቶ ጋዛሊ የፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሻሻል መድረኩ እያደረገ ላለው ጥረት በአመራርነት ዘመናቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባቸዋል ብሏል።
በክቡር አቶ ጋዛሊ አባሲማል ቦታ ለተተኩት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር ኦቶካና ኦዳ (ዶ/ር) መልካም የስራ ዘመን የተመኘው መድረኩ፣ የቀድሞው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ቀጣይ የሥራ ሕይወት ስኬታማ እንዲሆንላቸው መልካም ምኞቱን ገልጿል።




