ባሕር ዳር፣ መስከረም 30/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
በአገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ልዩ ጉባኤ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የቀጣይ ሦስት ዓመት የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ለውይይት ቀርቦ ጸድቋል።
ልዩ ጉባኤው በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ በመድረኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረትን ጨምሮ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈዋል።
በጉባኤው የቀረበው የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የሦስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና በመሠረታዊነት ለመለወጥ የተጀመሩ ጥረቶችን በተቀናጀ መንገድ ለማስቀጠል ያለመ ነው። ማዕቀፉ በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል ቅንጅትን በማጠናከር፣ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማስፋፋትና በቀደሙት የለውጥ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን ዘላቂ ለማድረግ መሠረት እንደሚሆን በጉባኤው ተነስቷል።
የፍርድ ቤቶች የጋራ ትብብርና የተቀናጀ አሠራር የዳኝነት አገልግሎቱን ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑም፣ የትራንስፎርሜሽን ማዕቀፊ ቀርቦ በጸደቀበት ወቅት ተገልጿል።
በዲጂታላይዜሽን የተደገፈ የዳኝነት አገልግሎትን እስከ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ድረስ በማስፋፋት የሕዝቡን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስና አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግም ሀገርአቀፍ የህግ ተርጓሚዎች መድረክ እና ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በጋራ ያዘጋዱት የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ትግበራ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
የሦስት ዓመቱ የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ መጽደቅ የፍርድ ቤቶችን የጋራ የለውጥ አቅጣጫ ለማስቀመጥና በቀጣይ ዓመታት የሚከናወኑ የማሻሻያ ሥራዎችን በተቀናጀ መንገድ ለመፈጸም መሠረት የሚጥል እርምጃ ነው።




