ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የጋራ የትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ፍርድ ቤቶችን በአንድ የለውጥ አቅጣጫ የሚያስተሳስር እና የዳኝነት ሥርዓቱን በተቀናጀ መንገድ ለማሻሻል የሚያግዝ ነው” ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

“የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የጋራ የትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ፍርድ ቤቶችን በአንድ የለውጥ አቅጣጫ የሚያስተሳስር እና የዳኝነት ሥርዓቱን በተቀናጀ መንገድ ለማሻሻል የሚያግዝ ነው” ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

ባሕር ዳር፣ መስከረም 30/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የሀገሪቱን የዳኝነት ሥርዓት ግልጽ፣ ተደራሽና ቀልጣፋ በማድረግ የዳኝነት አገልግሎትን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለውን የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የቀጣይ ሦስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ለማጽደቅ ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ልዩ ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ ሀገር አቀፉ መድረክ በክልሎች መካከል ያለውን ትብብርና ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ የፍርድ ቤቶችን አሠራር ለማሻሻል፣ የዳኝነት እሴቶችን ለማስፋፋትና የጋራ የለውጥ አቅጣጫ ለመቅረጽ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ እንዳስረዱት፣ መድረኩ በፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታና በሌሎች የፍርድ ቤት ማሻሻያ ሥራዎች ላይ ያለውን ተሞክሮ ለመለዋወጥ እድል ፈጥሯል።

በተለይም በእነዚህ ዘርፎች የተሻለ ልምድ ያካበቱ ፍርድ ቤቶች ልምዳቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ በማስቻል የአቅምና የቴክኖሎጂ ልውውጥ መድረክ ሆኗል።

ሁሉም የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዘላቂና ውጤታማ ለውጥ ለማምጣት በተናበበ መልኩ እንዲሠሩ የሚያግዘው ይህ መድረክ፣ የፍርድ ቤቶችን ሀብት በጋራ በመጠቀምና በትብብር በመሥራት በአገልግሎት ሰጪና ተገልጋይ መካከል ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍም አስፈላጊ መሆኑን ክቡር አቶ ቴዎድሮስ አመልክተዋል።

እንደ ክቡር ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፣ የዳኝነት አገልግሎቶችን የበለጠ ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ እንደ ኢ-ፋይሊንግና የቃለ መሐላ አገልግሎቶች ያሉ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ማስፋፋት፣ የሁሉም ክልሎችን የአቅም ልዩነት ያገናዘበ አሠራር መዘርጋትና አገልግሎቶች በተቀላጠፈ ሁኔታ ለሁሉም እንዲደርሱ መሥራት ይጠይቃል።

የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሥራ የጋራ አቅጣጫና የተደራጀ የአፈጻጸም ሥርዓት እንዲኖረው፣ የተሳኩና ያልተሳኩ ተሞክሮዎችን በመገምገም ጥንካሬዎችን ለማሳደግና ድክመቶችን ለማረም የትራንስፎርሜሽን ማዕቀፉ ወሳኝ መሣሪያ መሆኑንም አብራርተዋል።

ዛሬ ለውይይትና ለማጽደቅ የቀረበው የቀጣይ ሦስት ዓመት ማዕቀፍ፣ የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች በጋራ የለውጥ አቅጣጫ እንዲመሩ፣ የአሠራር ሥርዓታቸውን እንዲያጠናክሩና የዳኝነት አገልግሎቱን ግልጽ፣ ተደራሽና ቀልጣፋ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የማዕቀፉ ዝግጅትና አፈጻጸም የክልሎችን የአቅም ሁኔታ ያገናዘበ ከመሆን ባለፈ፣ ሁሉንም ፍርድ ቤቶች በአንድ የለውጥ አቅጣጫ የሚያስተሳስር መሆኑ የዳኝነት ሥርዓቱን በተቀናጀ መንገድ ለማሻሻል ያለውን ፋይዳ ያሳያል።

የሀገር አቀፉ ጉባኤ ቀጣይነት ተጠብቆ ውይይቶችና የልምድ ልውውጦች በተከታታይ እንዲካሄዱ ማድረግ፣ የማዕቀፉ ተግባራዊነት ለማረጋገጥና የፍርድ ቤቶችን የጋራ አቅም ለማጠናከር አስፈላጊ መሆኑም በመልዕክቱ ተጠቁሟል።

በጉባኤው ላይ የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈዋል።

የሀገር አቀፉ የሕግ ተርጓሚዎች ልዩ ጉባኤ ዓላማ የፍርድ ቤቶችን የጋራ ራዕይ ማጠናከር፣ የተሻሉ ተሞክሮዎችን ማስፋፋትና በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሚከናወኑ የለውጥ ሥራዎችን በጋራ አቅጣጫ ለማስኬድ መሠረት መጣል ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *