ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“ቅልጥፍናና ጥራት አብረው መሄድ አለባቸው” — ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው

“ቅልጥፍናና ጥራት አብረው መሄድ አለባቸው” — ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው

ባሕር ዳር፤ መስከረም 29/ 2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የዳኝነት አገልግሎት በጊዜው ከመሰጠቱ ጋር የውሳኔዎች ጥራትም መጠበቅ እንዳለበት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ገልጸዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ ይህን የገለጹት “የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል ለአሥር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ በቆየው ሁለተኛው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ክቡር አቶ አለምአንተ የዳኝነት አገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ተጣምረው መሄድ እንዳለባቸው ሲያስገነዝቡ፣ “ጥራቱ የተጠበቀ ውሳኔ በጊዜው ካልደረሰ ለተጎጂው ዋጋ ያጣል፤ በጊዜው የደረሰ ውሳኔም ጥራት ከሌለው ፍትሕ አይሆንም። ስለዚህ ቅልጥፍና እና ጥራት አብረው መሄድ አለባቸው” ብለዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፣ የዳኝነት ነጻነትና ተጠያቂነት በሚዛናዊነት መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ ዳኛ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ሕግንና ሕሊናውን ብቻ በመከተል ውሳኔ መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል። በዳኝነት ሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮችም ተገቢውን ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የዳኝነት ሙያ ከሕግ ዕውቀት ባሻገር የሕሊና፣ የሐቀኝነትና የትሕትና ሙያ መሆኑን ያስታወሱት ክቡር ፕሬዝደንቱ ፣ የሕዝብ አመኔታ የሚገነባው በሚሰጡት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በዳኞች የዕለት ተዕለት አኗኗርና ሥነ-ምግባርም ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ከሙስናና ከአድሏዊ አሠራር በመራቅ የሙያውን ክብር መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ በተለይም በወረዳ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ውሳኔዎችን ጥራት ማሻሻል የቀጣይ ጊዜ ዋነኛ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፣ ኅብረተሰቡ ከፍርድ ቤቶች ጋር የሚኖረው የመጀመሪያና አብዛኛው ግንኙነት በወረዳ ፍርድ ቤቶች በኩል እንደሆነ አስታውሰዋል። ስለዚህ የወረዳ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ጥራት የመላው የዳኝነት ሥርዓቱን ጥራት እንደሚወስን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የሚያደርጉትን ክትትልና ድጋፍ እንዲያጠናክሩ፣ ዳኞችም በጉባኤው ያገኙትን ዕውቀት በሥራ ቦታቸው በተግባር እንዲያውሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት የበለጠ ተደራሽ ለማድረግም ዲጂታላይዜሽንን ማስፋፋት፣ የኤሌክትሮኒክ አቤቱታ አቀራረብና የርቀት ችሎት አገልግሎቶችን ማጠናከር፣ እንዲሁም በእርቅ፣ በሽምግልናና በፍርድ ቤት-መር አስማሚነት ሊፈቱ የሚችሉ ክርክሮች በአማራጭ የፍትሕ ሥርዓቶች እንዲፈቱ ማበረታታት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዳኞች የተማሩትን አዳዲስ ሕጎች በሥራቸው እንዲተገብሩ፣ የመዝገብ አያያዝና የቀጠሮ አሰጣጥ ሥርዓትን እንዲያጠናክሩ፣ የዳኝነት ሥነ-ምግባርን እንዲጠብቁና ባለጉዳዮችን በትሕትናና በአክብሮት እንዲያስተናግዱም አሳስበዋል።

ክቡር አቶ አለምአንተ፣ በመዝጊያ ንግግራቸው፣ የዳኝነት ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት በንግግር ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በሚሰጡ ውሳኔዎች፣ በሚታየው ሥነ-ምግባርና በሥራ ትጋት መገለጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *