ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች እያሳዩት ያለው ለውጥ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው” ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

“የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች እያሳዩት ያለው ለውጥ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው” ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

ባሕር ዳር፣ መስከረም 29/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እያሳዩት ያለው መሻሻልና ለውጥ በቁርጠኝነት፣ በቅንነትና በተቀናጀ ጥረት የተቋማትን አቅም ማሳደግና ውጤታማ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ ምሳሌ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን የገለጹት ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ በቆየው ሁለተኛው የአማራ ክልል ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ የመዝጊያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። በመዝጊያ መርሐ ግብሩ ላይ የሌሎች ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፣ በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የታዩት ለውጦች በፍትሕ አገልግሎት ተደራሽነት፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናና ለሥራ ምቹ የሆነ አካባቢ በመፍጠር የታዩ እመርታዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው፣ “የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እያሳዩ ያሉት መሻሻልና ለውጥ ምሳሌ ሊሆን የሚችል፣ የሰው ልጅ አቅዶ በቅንነት ከሠራ ያለበትን ሁኔታ ለመለወጥ ያለውን አቅም የሚያሳይ ነው።” ብለዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፣ የተገኙት ውጤቶች የአመራር ቁርጠኝነት፣ የክልሉ መንግሥት ለዳኝነት አካሉ የሰጠው ትኩረትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ውጤት ናቸው። በመሆኑም የተጀመሩትን የለውጥ ሥራዎች ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ መንግሥት ለፍርድ ቤቶች በጀት በመመደብና አስፈላጊ ሕጎችን በማውጣት ያደረገው ድጋፍ ለተገኙት ውጤቶች ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፣ ይህ ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል፣ የፍርድ ቤቶችን የዲጂታላይዜሽን ሥራ ለማስፋፋት በተለያዩ የፍትሕ ተቋማት መካከል ያለው ትብብር መጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል። በዚህ ረገድ ድምጽን ወደ ጽሑፍ የሚቀይር ቴክኖሎጂ፣ የርቀት ችሎት አገልግሎትና የኤሌክትሮኒክ ክስ ማቅረቢያ ሥርዓት የፍትሕ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽና ቀልጣፋ ከማድረግ ባለፈ የፍርድ ቤቶችን ተዓማኒነት ለማጠናከር እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ ገልጸዋል።

እነዚህን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምዶች በማስፋትና በማስቀጠል፣ ዜጎች በቅርባቸው፣ በአነስተኛ ወጪና ጥረት መብታቸውን ማስከበር የሚያስችል የፍትሕ ሥርዓት በመላ አገሪቱ ማስፋፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ፕሬዝዳንቱ የዳኝነት ሥራ ከፍተኛ የሞራል ልዕልና፣ የሥነ ምግባር ቁርጠኝነትና ሙያዊ ብቃት የሚጠይቅ ኃላፊነት መሆኑንም አስረድተዋል። ዳኞች ሁሉንም ሰው በእኩልነት ማስተናገድ፣ ከወገንተኝነት መራቅና ውሳኔዎቻቸውን በሕግና በማስረጃ ላይ ብቻ በመመሥረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።

የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት የፍትሕ ሥርዓቱ መሠረታዊ መርሆዎች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ነጻነቱን መጠበቅ የዳኞች የግል ኃላፊነት ቢሆንም ይህ ነጻነት እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የመንግሥትና የተቋማት ድርሻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የዳኞች ሙያዊ ብቃት በመደበኛ ትምህርት ብቻ የሚገኝ ሳይሆን፣ አዳዲስ ሕጎችንና የሕግ ጽንሰ ሐሳቦችን በመከታተል፣ ዕውቀትን በማዳበርና ሙያዊ ክህሎትን በቀጣይነት በማሳደግ የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የዳኞች ሥልጠናዎች ሙያዊ ብቃትን ለማጠናከርና የዜጎችን የፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ያላቸውን ሚና አጉልተዋል።

በመጨረሻም ዳኞች የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ፍትሕን ለማስፈን የሚወጡት ኃላፊነት ከፍተኛ ማኅበራዊና ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንን ኃላፊነት በቁርጠኝነት ለሚወጡ ዳኞች እውቅናና ምስጋና አቅርበዋል። ዳኞች በቀጣዩ የሥራ ዘመን የተሸከሙትን ከባድ ኃላፊነት በብቃትና በሥነ ምግባር እንዲወጡ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአማራ ክልል ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ፣ የዳኞችን ሙያዊ ብቃት ለማሳደግ፣ የዳኝነት አገልግሎትን ለማሻሻልና በፍትሕ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *