ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቀቀ

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ባሕር ዳር፤ መስከረም 29/ 2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

ከ2,000 በላይ የአማራ ክልል ዳኞችን በአንድ መድረክ ያሰባሰበውና “የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል ለአሥር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።

በጉባኤው የክልሉ ፍርድ ቤቶችን የሙያ ብቃትና ተቋማዊ አቅም ለማጎልበት፣ የዳኝነት ሥነ-ምግባርን ለማጠናከር፣ የፍትሕ አሰጣጥን ቅልጥፍናና ጥራት ለማሻሻል እንዲሁም የዳኝነት አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችሉ ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ሥልጠና ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በጉባኤው መዝጊያ ንግግራቸው፣ ዳኞች ባሳዩት ንቁና ገንቢ ተሳትፎ ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸው፣ የጉባኤው ዋና ዓላማ የሙያ ዕውቀትን ማሳደግ፣ በቁልፍ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠርና ሙያዊነትን ማጎልበት መሆኑን አስታውሰዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ በ2018 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያ ዓመታዊ ጉባኤ የተገባውን የባሕር ዳር ቃል ኪዳን በመጠበቅ በበጀት ዓመቱ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች አመርቂ የሥራ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቅሰዋል። ይህም የዳኞችን ትጋትና ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ በተገኙ ውጤቶች ሳይዘናጉ ቀሪ ተግባራትን በትኩረት ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአሥሩ ቀናት የጉባኤ መርሐ ግብር የዳኝነት ሥነ-ምግባር፣ አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት፣ የመሬትና የንግድ ሕጎች፣ የንግድ ድርጅቶችና የኪሳራ ሕግ፣ የኢንቨስትመንትና የልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሕጎች፣ የካፒታል ገበያ ሥርዓት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ዲጂታላይዜሽንና ፍርድ ቤት-መር አስማሚነት በዋናነት ተዳስሰዋል።

በተጨማሪም የፍርድ ቤቶችን የአመራር ብቃትና ተቋማዊ ማሻሻያ ለማጠናከር የተዘጋጁ የዕቅድ አፈጻጸምና የክትትል ሪፖርቶች፣ የመዋቅር ጥናትና የተቋሙን ቀጣይ የለውጥ አቅጣጫ የሚመለከቱ ሰነዶች ለውይይት ቀርበው ግብዓት ተሰብስቧል።

በጉባኤው የዳኝነት ነጻነትና ተጠያቂነትን በሚዛናዊነት ማስኬድ፣ የውሳኔ አሰጣጥን ጥራትና ቅልጥፍና ማሻሻል፣ የዳኞችን ቀጣይ ሙያዊ ዕድገት ማረጋገጥና በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች መካከል የተሻለ ቅንጅት መፍጠር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ ግንዛቤ ተፈጥሯል።

ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣በተለይም በወረዳ ፍርድ ቤቶች የውሳኔ ጥራትን ማሻሻል፣ የዳኞችን የሥራ አቅም ማጎልበት፣ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋትና የከፍተኛ ፍርድ ቤቶችን የክትትልና ድጋፍ ሥራ ማጠናከር ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተጨማሪም የክልሉ ፍርድ ቤቶች በዲጂታል የፍትሕ አሰጣጥ፣ በኢ-ፋይሊንግ፣ በስማርት ችሎትና በቪዲዮ ኮንፈረንስ አጠቃቀም ረገድ የጀመሩትን ለውጥ ማስፋፋት፣ ባለጉዳዮች በ6152 የጥሪ ማዕከልና በሞባይል መተግበሪያ የሚያገኙትን አገልግሎት ማሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ የተገኘው ዕውቀትና የተወሰዱ ትምህርቶች በየፍርድ ቤቱ ወደ ተግባር እንዲቀየሩ፣ የዳኝነት ሥነ-ምግባርና ተጠያቂነት እንዲጠናከሩ እንዲሁም የሕዝብን አመኔታ የሚያሳድግ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ጥራቱ የተጠበቀ የዳኝነት አገልግሎት ለማረጋገጥ ጥሪ በማቅረብ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *