ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣንና አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ምንነትና አገልግሎት ላይ ለክልሉ ዳኞች ገለጻ ተደረገ

በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣንና አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ምንነትና አገልግሎት ላይ ለክልሉ ዳኞች ገለጻ ተደረገ

ባሕር ዳር፣ መስከረም 27/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት አገልግሎቶች እንዲሁም ተቋማቱ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር ባላቸው መስተጋብር ላይ ለክልሉ ዳኞች ገለጻ ተደርጓል።

ገለጻው የካፒታል ገበያን ምንነት፣ የካፒታል ገበያ ባለስልጣንን የሕግ መሠረትና ተግባራት፣ የኢንቨስተሮች ጥበቃ፣ የሰነድ መዋለ ንዋይ ምዝገባና ግብይት እንዲሁም የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሥልጣንና ተግባራትን ያካተተ ነበር።

ገለጻውን የሰጡት ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እና ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የመጡ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ የካፒታል ገበያ ሻጭና ገዥ የሚገናኙበት የግብይት ሥርዓት መሆኑ ተብራርቷል።

ባለሙያዎቹ በገለጻቸው፣ የሰነድ መዋለ ንዋይ ምዝገባ አስፈላጊነት፣ ለምዝገባ መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች፣ ለሕዝብ ሊቀርቡ የሚችሉና በልዩ ሁኔታ የማይመዘገቡ የሰነድ መዋለ ንዋዮች እንዲሁም ብቁ አልሚዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጠዋል።

ገለጻውን ተከትሎ በተካሄደ የፓናል ውይይትም የኢንቨስተሮች ጥበቃ፣ የመረጃ ተደራሽነት፣ የሰነድ መዋለ ንዋይ ምዝገባ፣ የተመዘገቡ ድርጅቶች ወደ ገበያው የሚገቡበት ሂደትና ለግብይት የሚያቀርቡት ሰነደ መዋለ ንዋይ የተመለከቱ ጉዳዮች ተነስተዋል።

በተጨማሪም የገበያውን ታማኝነት ለመጠበቅ የተከለከሉ የንግድ ተግባራት፣ የውስጥ አዋቂ ግብይት፣ የገበያ ማጭበርበርና የሐሰት ግብይት መፍጠርን ጨምሮ ሕገወጥ የግብይት ተግባራት በሚያስከትሉት የሕግ ተጠያቂነት ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በዚህም የኢንቨስተሮችን ንብረት ከጉዳት መጠበቅ፣ ከማጭበርበር መከላከል፣ የገበያውን ታማኝነት ማስጠበቅና በገበያው ተሳታፊዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በሕጋዊ ሥርዓት መፍታት የኢንቨስትመንት አካባቢውን እምነት የሚያሳድጉ ተግባራት መሆናቸው ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ላይ የተሰጠው ገለጻ በፍርድ ቤቱ ሥልጣንና ተግባር፣ አወቃቀር፣ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ያለውን ልዩነትና መስተጋብር እንዲሁም በካፒታል ገበያ የሚፈጠሩ ክርክሮችን በሚፈታበት ሥርዓት ያተኮረ ነበር።

ባለሙያዎቹ እንደገለጹት፣ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ የካፒታል ገበያው ልዩ ባህሪና ውስብስብነት በመኖሩ፣ በገበያው ውስጥ ፈጣን ውሳኔ መስጠት በማስፈለጉ እና የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የጉዳይ ፍሰት ለመቀነስ በሚያስችለው ሁኔታ ልዩ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም ነው።

አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ እንደማንኛውም ፍርድ ቤት ማስረጃና መረጃ በመመርመር፣ ባለጉዳዮችን በማከራከርና በጉዳዩ ላይ ውሳኔ በመስጠት የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል። በፍሬ ነገር ጉዳዮችም የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት ሥልጣን እንዳለው ተብራርቷል።

አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የሕግ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ አስተማሪ የሕግ ጽሑፎችን ተደራሽ ለማድረግ እና ለሕግ ባለሙያዎች፣ ለአቃቢ ሕጎችና ለወንጀል መርማሪዎች ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ተቋሙ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር ያለውን ትብብርና ቅንጅት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ ከስምንት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በጋራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በገለጻው የኢንቨስተሮች ጥበቃ ከካፒታል ገበያ አንጻር ያለው ሚናም በስፋት ተነስቷል። ኢንቨስተሮች የመዋዕለ ንዋያቸውን ውሳኔ በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው እንዲያደርጉ፣ ከማጭበርበር እንዲጠበቁና መብቶቻቸውን እንዲያገኙ የመረጃ ተደራሽነትና የሕግ ጥበቃ ወሳኝ መሆኑ ተብራርቷል።

የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴን የሚመሩ የሕግ ማዕቀፎችን እና የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱን ሥልጣንና ተግባር ማስተዋወቅ ለዳኞች በዘርፉ የሚነሱ ጉዳዮችን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳትና በተቋማት መካከል ያለውን የሕግ መስተጋብር ለማጠናከር ያለው ጠቀሜታ ተጠቁሟል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *