ባሕር ዳር፣ መስከረም 27/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
“የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ለሚገኘው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ተሳታፊ ዳኞች በኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ የፍርድ ቤቶች ሚና በሚል ርዕስ ገለጻ ተደርጓል።
ገለጻውን ያቀረቡት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካርያስ ቀነአ ሲሆኑ፣ የኢንቨስትመንት ምንነትና ባሕሪያት፣ ከኢንቨስትመንት የሚመነጩ አለመግባባቶች፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ሕጎች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ለመፍታት ፍርድ ቤቶች ያላቸውን ሚና በስፋት አብራርተዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰሩ እንዳብራሩት፣ የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ከተለያዩ ወገኖች እና ተቋማት ጋር የተሳሰሩ በመሆኑ በአልሚዎች፣ በመንግሥት አካላትና በሌሎች ተዋናዮች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የተለየ የሕግ እውቀትና ጥንቃቄ የሚጠይቁ ናቸው።
በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚመለከቱ አለመግባባቶች የሀገር ውስጥ ሕጎችን ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ሕግ መርሆዎችን ጭምር ታሳቢ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ ባለብዙ ወገንና በሁለት ሀገራት መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና ስምምነቶች በኢንቨስትመንት አለመግባባቶች አፈታት ውስጥ ያላቸው ሚና ተገልጿል።
ከዚህ አንጻር የፍርድ ቤቶች ሚና የሚጀምረው ኢንቨስትመንትን ከሚመለከቱ ሕጎችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተያያዘ የተሟላ የሕግ እውቀት ከመያዝ እንደሆነ በገለጻው ተጠቁሟል።
ዳኞች የኢንቨስትመንት ሕጎችን፣ የአርቢትሬሽን ሥርዓቶችንና ተያያዥ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በበቂ ሁኔታ መረዳታቸው የሚመጡ የኢንቨስትመንት ጉዳዮችን በሕግና በማስረጃ ላይ በመመሥረት ለመዳኘት ወሳኝ መሆኑ ተብራርቷል።
የኢንቨስትመንት አለመግባባቶች በድርድርና በውይይት እንዲፈቱ ቅድሚያ የሚሰጥ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ወደ አርቢትሬሽን ሲሄድም የፍርድ ቤቶች ሚና የሚያበቃ እንዳልሆነ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካርያስ ገልጸዋል።
በተለይም ፍርድ ቤቶች ጊዜያዊ ትዕዛዝ በመስጠት፣ በአርቢትሬሽን ትራይቡናል ምስረታ ላይ ድጋፍ በማድረግ፣ አስፈላጊ ማስረጃ እንዲሰበሰብ በማገዝ፣ የአርቢትሬሽን ውሳኔዎችን እውቅና በመስጠትና በማስፈጸም እንዲሁም በሕግ በተፈቀደ ወሰን የፍርድ ቤት ክለሳ በማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተብራርቷል።
“በአርቢትሬሽን ሂደት የፍርድ ቤቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑ እና የፍርድ ቤቶች ድጋፍ አርቢትሬሽን ውጤታማና ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያስችል መሠረታዊ ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል።
ሆኖም ይህ ድጋፍ የአርቢትሬሽን ሂደትን በመተካት ሳይሆን፣ በሕግ በተወሰነው ወሰን ብቻ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የውጭ አልሚዎች በሀገሪቱ ውስጥ ያላቸውን መብትና ጥቅም በፍርድ ቤት ለማስከበር የሚያስችል የሕግ ሥርዓት መኖሩ የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል። በዚህም ፍርድ ቤቶች የኢንቨስትመንት አካባቢ የሕግ የበላይነትን፣ የውሳኔ ተፈጻሚነትንና የባለሀብቶችን የሕግ ጥበቃ በማረጋገጥ አስፈላጊ ተቋማዊ ሚና እንዳላቸው ተነስቷል።
በገለጻው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ሕግ ማዕቀፎች ያላት ተሳትፎ፣ በተለይም በባለብዙ ወገን የኢንቨስትመንት ስምምነቶችና ተቋማት ያላት ተሳትፎ እንዲሁም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን በተመለከተ ያደረገቻቸው ተሳትፎዎች ተነስተዋል። እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች የኢንቨስትመንት ጉዳዮችን በሚመለከት ለዳኞች የተለየ የሕግ እውቀት እንደሚጠይቁ ተገልጿል።
በመጨረሻም፣ ኢንቨስትመንት እየተሳሰረና የንግድ ግንኙነቶች ከሀገር ወሰን እየተሻገሩ በመጡበት ወቅት፣ ፍርድ ቤቶችና ዳኞች ከሀገር ውስጥ የኢንቨስትመንት ሕጎች ባሻገር ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ሕግን፣ አርቢትሬሽንን እና የውሳኔ አፈጻጸም ሥርዓቶችን በበቂ ሁኔታ መረዳትና ለሚመጡ ጉዳዮች ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
በርእሰ ጉዳዩ ላይ የቀረበው ገለጻ የክልሉ ዳኞች በተለያዩ የሕግ ዘርፎች እየተሰጣቸው ካለው የእውቀትና የክህሎት ግንባታ ሥልጠና ጋር ተያይዞ፣ ዳኞች በዘመናዊና ውስብስብ የሕግ ጉዳዮች ላይ በቂ እውቀትና ብቃት እንዲኖራቸው ለማስቻል የሚደረገውን ተቋማዊ ጥረት የሚያጠናክር ነው።







