ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በኢንቨስትመንትና በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሕጎች ላይ ለክልሉ ዳኞች ስልጠና ተሰጠ

በኢንቨስትመንትና በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሕጎች ላይ ለክልሉ ዳኞች ስልጠና ተሰጠ

ባሕር ዳር፣ መስከረም 26/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

በአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሕጎችና በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሕግ ዙሪያ ለክልሉ ዳኞች ስልጠና ተሰጠ።

ስልጠናውን የሰጡት የአባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ታደሰ ካሳ ሲሆኑ፣ በተለይም በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ የተካሄዱ የኢኮኖሚና የሕግ ማሻሻያዎች፣ የኢንቨስትመንት ሕጎች የተሻሻሉበት ምክንያት፣ የባለሀብቶች መብትና ግዴታ እንዲሁም የልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሕግ ማዕቀፍ ላይ ሰፊ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዶ/ር ታደሰ በገለጻቸው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማዕቀፍ በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት የተካሄዱ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት አድርገዋል። ማሻሻያዎቹ ዋና ዓላማ የኢኮኖሚ እድገትንና የሀገሪቱን ተወዳዳሪነት ማጠናከር፣ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተገማች የሕግ ሥርዓት መፍጠር እና ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አሰልጣኙ ገለጻ፣ ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን ከማሻሻል ባሻገር ተቋማዊና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማካሄድ ያስፈልጋል። በዚህም ሂደት የንግድ ሕግን ጨምሮ በርካታ ሕጎች እንዲወጡና ነባር ሕጎች እንዲሻሻሉ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀት ብቻ የኢንቨስትመንት ሥርዓቱን ውጤታማ አያደርገውም ያሉት ዶ/ር ታደሰ፣ የሕጎቹ አፈጻጸም ግልጽ፣ ተገማችና ወጥ እንዲሆን የተቋማት አሠራርና የፍትሕ ሥርዓቱ በተመጣጣኝ ደረጃ መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የሕግ ሥርዓቱ ወደ ተገማችና የተረጋጋ አሠራር መሸጋገሩ ለኢንቨስትመንት እምነት መገንባት ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የውጭና የአገር ውስጥ ካፒታልን ለመሳብ ያላትን ዕድል ለመጠቀም የኢንቨስትመንት ሕጎቿ አስቻይ፣ ግልጽና ተገማች መሆን እንዳለባቸውም ተገልጿል። በዚህ ረገድ የግሉን ዘርፍ የሚያበረታቱ የሕግ ማዕቀፎችን መዘርጋት፣ የተቀናጀ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ሥርዓት መፍጠርና በኢንቨስትመንት ሂደት ያሉ ማነቆዎችን መቅረፍ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በስልጠናው ከኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ጋር በተያያዘ የፈቃድ እገዳ፣ መሰረዝና መንጠቅ ሂደቶች እንዴት እንደሚመሩ በዝርዝር ተብራርቷል።

የስልጠናው ሌላው ክፍል በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሕግ ላይ ያተኮረ ነበር። የልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሕግ አስፈላጊነት ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነቶች፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከነጻ የንግድ ቀጠናዎች ጋር በማያያዝ ተብራርቷል።

በዚህ ዙሪያ የልዩ የኢኮኖሚ ዞን ስያሜ ለማግኘት የሚያስፈልጉ ሰነዶች፣ ባለብዙ ዘርፍና የተለየ የኢኮኖሚ ዞን አመዳደብ፣ የዞኑ መሬት ምደባ፣ ልማትና አጠቃቀም እንዲሁም ለመሬት፣ ለሕንፃና ለንብረት የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ አሰጣጥ በሕግ የተቀመጡ መርሆዎች በዝርዝር ቀርበዋል።

ዶ/ር ታደሰ እንዳብራሩት፣ የኢንቨስትመንት ሕጎች የኢኮኖሚ ፖሊሲን ብቻ የሚደግፉ የሕግ ሰነዶች ሳይሆኑ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን፣ የባለሀብቶችን እምነት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ እና የፍትሕ ሥርዓቱን ተገማችነት የሚወስኑ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ሕግ ማዕቀፎች ናቸው።

ስልጠናው ዳኞች የኢንቨስትመንትና የልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሕጎችን በተግባር ለመተርጎምና ለመተግበር ያላቸውን የሕግ እውቀት ለማጎልበት እና በኢንቨስትመንት ክርክሮች ላይ ግልጽ፣ ወጥና ተገማች የፍትሕ አሠራርን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *