ባሕር ዳር፣ መስከረም 26/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
በተለያዩ የዳኝነት እና የፍትሕ ጉዳዮች ላይ የክልሉን ዳኞች አቅም ለማጎልበት የሚሰጡ ስልጠናዎች ቀጥለው ውለዋል።
በጉባኤው የዛሬ ውሎም፣ “የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ትግበራ በፌዴራል እና የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ” በሚል ርዕስ ለክልሉ ዳኞች ገለጻ ተደርጓል።
ገለጻውን ያደረጉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ልዩ አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ እና ዶክተር ዮናስ ግርማ ናቸው።
በስልጠናው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ጽንሰ ሀሳብ፣ የሕግ ማዕቀፉ፣ ከመደበኛው የዳኝነት ሥርዓት ጋር ያለው መስተጋብር፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተሞክሮ እና በአማራ ክልል በሙከራ ደረጃ የሚከናወነው ትግበራ በስፋት ቀርቧል።
ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ በገለጻቸው፣ በአማራ ክልል በጅምር ትግበራ ላይ የሚገኘውን የፍርድ ቤት መር አስማሚነት አፈጻጸም ለመገምገም የተካሄደ ዳሰሳ ጥናት ውጤት አቅርበዋል።
ጥናቱ የሙከራ ትግበራው አሁን ያለበትን ደረጃ፣ የታዩ አዎንታዊ ጎኖች፣ ያጋጠሙ ክፍተቶችና ችግሮች እንዲሁም በቀጣይ ሊሠሩ የሚገቡ ጉዳዮችን ለመለየት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ትግበራ አስፈላጊነትን ሲያብራሩም፣ የፍትሕ አገልግሎትን ማስፋትና ለህብረተሰቡ የፍትሕ ማግኛ አማራጮችን ማብዛት በማስፈለጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመደበኛው የፍርድ ቤት አሠራር ብቻ ለሁሉም ህብረተሰብ የፍትሕ ፍላጎቶች ላይ ፈጣንና ውጤታማ መፍትሔ ማምጣት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት እንደ አማራጭ የፍትሕ መስጫ ሥርዓት ሊያገለግል እንደሚችልም አስረድተዋል።
አስማሚነት በተፈጥሮ በሰዎች ግንኙነት፣ በቤተሰብ፣ በማህበራዊ እና በሌሎች የግንኙነት መስኮች ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሚመነጩ ግጭቶችን በመነጋገርና በመስማማት ለመፍታት የሚያግዝ ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የፍርድ ቤቶችን ጫና መቀነስ ከሚገኙ ጥቅሞች አንዱ እንጂ ዋናው ዓላማ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ዋናው ትኩረት የፍትሕ ተገልጋዮችን ጊዜ፣ ወጪና ጫና መቀነስ እና ተወያይተው በራሳቸው ፈቃድ መፍትሔ እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑን አስገንዝበዋል።
በገለጻቸው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ዋና ዋና መርሆዎች፣ አስማሚው ሊኖሩት የሚገቡ ብቃቶችና መመዘኛዎች፣ እንዲሁም አስማሚነት ከመደበኛው የዳኝነት ሥራ ጋር እንዴት ሊቀናጅ እንደሚችል በዝርዝር ቀርቧል።
በተመሳሳይም፣ ዶክተር ዮናስ ግርማ፣በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ያለውን የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓትና የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በማነጻጸር አቅርበዋል።
እንደ ገለጻቸው፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት በፈቃደኝነት ወይም በሕግ በተወሰነ ሁኔታ በግዴታ ወደ አስማሚነት ሂደት የሚገባበት መልክ ሊኖረው የሚችል ሲሆን፣ የትኞቹ ጉዳዮች በግዴታ ሂደቱ ውስጥ እንደሚገቡና የትኞቹ እንደማይገቡ በግልጽ መለየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በአስማሚነት ሂደት የሚከበሩ መርሆዎች መካከልም ሚስጥራዊነት፣ ገለልተኝነትና የተሳታፊዎችን ፈቃደኝነት ማክበር ዋና መርሆዎች መሆናቸውን አብራርተዋል። ሂደቱ በሕግ አስገዳጅ ቢሆንም ተሳታፊዎች በአስማሚው ላይ ያለፈቃዳቸው የሚያስማማ ጫና እንዳይደረግባቸው መጠበቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተሞክሮን በማብራራትም፣ በቂ ስልጠና የወሰዱ አስማሚዎች በሥርዓቱ ውስጥ እንደሚሳተፉ፣ ዳኞች ግን በቀጥታ አስማሚ ሆነው እንደማይሠሩ ገልጸዋል። ይህም በአስማሚነት ሂደት የሚገኘው መረጃ ከመደበኛው የዳኝነት ሂደት ጋር ተደባልቆ እንዳይጠቀም ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ለፍርድ ቤት መር አስማሚነት የተለየ ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖረው፣ ለፍርድ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የአስማሚነት አስተባባሪ ቢሮ እና የሚያስፈልጉ የሰው ኃይልና የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋት እንደሚገባ ተገልጿል።
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ የአስማሚነት ሂደት ከክስ ሂደቱ ጋር ተቀናጅቶ የሚካሄድ ሲሆን፣ ባለጉዳዮች በተወሰነላቸው ጊዜ በአስማሚነት ማዕከል በመቅረብ ጉዳያቸውን በውይይት እንዲፈቱ የሚያስችል አሠራር መኖሩንም ገልጸዋል።
በመጨረሻም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአስማሚነት ሥርዓት በሙከራ ትግበራና በሙሉ ትግበራ ሁለት ዋና የትግበራ ምዕራፎችን አልፎ መጠናከሩን በማስታወስ፣ በሁለቱም ወቅቶች የታዩ ጠንካራ ጎኖችና ያጋጠሙ ችግሮች በአማራ ክልል ለሚካሄደው የሙከራ ትግበራ ጠቃሚ ተሞክሮ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
በርእሰ ጉዳዩ ላይ ተሳታፊ ዳኞች አስተያይታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ጥያቄዎችንም አንስተው በአቅራቢዎቹ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጦባቸዋል።
የስልጠናው ዓላማ የክልሉ ዳኞች ስለ ፍርድ ቤት መር አስማሚነት ያላቸውን ግንዛቤና አቅም በማሳደግ፣ በክልሉ የተጀመረው የሙከራ ትግበራ የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዝ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ሲሆን፣ ጉባኤው ነገም በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ሲመክር ይውላል።











