ባሕር ዳር፣ መስከረም 25/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
በአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ዳኞች የሙያ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ፣ ተጨማሪ ንባብና ጥናት እንዲያደርጉ እንዲሁም የጋራ ተቋማዊ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ የሚያግዙ ስልጠናዎች፣ ገለጻዎችና ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው።
በዛሬው የጉባኤው ውሎም፣ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የዲጅታላይዜሽን ትግበራ ሂደት፣ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ ህጎች ላይ እንዲሁም የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ አቤቱታ አቀራረብና ሙግት መመሪያ ረቂቅ ላይ ገለጻና ውይይት ተካሂዷል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአይ.ሲ.ቲ ዳይሬክተር መኳንንት አገአሁ (ዶ/ር) በክልሉ ፍርድ ቤቶች የተከናወኑ የዲጅታላይዜሽን ሥራዎችን በተመለከተ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።
እንደ ዶ/ር መኳንንት ገለጻ፣ የቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት የሰው ልጆችን፣ ተቋማትንና የሥራ አሠራሮችን በፍጥነት እየቀየረ በመሆኑ ፍርድ ቤቶችም ከዚህ ለውጥ ውጭ ሊሆኑ አይችሉም። በተለይም ዲጅታላይዜሽን የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ፣ ፈጣንና ውጤታማ ከማድረጉም በላይ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው።
የፍርድ ቤቶች ዲጅታላይዜሽን ሥራ ለማስተባበር የዲጅታላይዜሽን ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ፍኖተ ካርታው ምን ምን የፍርድ ቤት ሥራዎች ዲጅታላይዝ መደረግ እንዳለባቸውና የሥራው አፈጻጸም አቅጣጫ እንዲለይ አስችሏል ብለዋል።
በአፈጻጸሙም የኔትወርክና የዳታ ማዕከል መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ዘመናዊ ችሎቶችና የርቀት ሙግት አገልግሎት፣ የደህንነት ካሜራዎችና የተለያዩ የሶፍትዌር ልማት ስራዎች መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ 14 ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ 27 ወረዳ ፍርድ ቤቶችና ሁለት ማረሚያ ቤቶች በዲጅታል መሠረተ ልማት መታገዛቸውንም ጠቁመዋል።
ከተዘረጉት የዲጅታል መፍትሔዎች መካከል የኤሌክትሮኒክስ አቤቱታ አቀራረብ (e-filing)፣ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ፣ የማሳወቂያ ሥርዓት፣ የችሎት ድምጽን ወደ ጽሑፍ የሚቀይር የትራንስክሪፕሽን ሶፍትዌር፣ የሞባይል መተግበሪያና የድረ-ገጽ አገልግሎቶች ይገኙበታል።
ኢ-ፋይሊንግ ባለጉዳዮች ባቅራቢያቸው ባሉ ፍርድ ቤቶች ሆነው አቤቱታቸውን በኤሌክትሮኒክስ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ሲሆን፣ የማሳወቂያ ሥርዓቱ ደግሞ ለዳኞችና ለባለጉዳዮች ተዛማጅ መረጃዎችን በወቅቱ እንዲደርሱ ያግዛል። የሞባይል መተግበሪያውም ባለጉዳዮች በስማቸው ወይም በመዝገብ ቁጥራቸው የጉዳያቸውን ሁኔታና ቀጠሮ እንዲከታተሉ ያስችላል።
በተጨማሪም የዕውቀት አስተዳደር ሥርዓት፣ ዲጅታል ቤተ-መጻሕፍትና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዲጅታል ሙዚየም መዘርጋታቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ልዩ አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ፣ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ አዋጆች ማሻሻያ እና የኤሌክትሮኒክስ አቤቱታ አቀራረብና ሙግት መመሪያ ረቂቆችን አስመልክቶ ገለጻ አቅርበዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ፣ የማሻሻያው አስፈላጊነት፣ የማሻሻያ ረቂቁ የተዘጋጀበትን ሁኔታ፣ በአዋጆቹ ማሻሻያ የሚደረግባቸው አንኳር ጉዳዮች እንዲሁም የተዘጋጁ ማሻሻያዎችን ለጉባኤው ተሳታፊ ዳኞች አቅርበዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ፣ ከዚህ በተጨማሪም፣ የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ አቤቱታ አቀራረብና ሙግት መመሪያ ረቂቅን በተመለከተ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የመመሪያው አስፈላጊነት፣ ረቂቁን ለማዘጋጀት የተደረጉ ጥረቶችና የተጠቀሱ ምንጮች እንዲሁም በረቂቁ የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች በገለጻው ተካተዋል።
በተደረጉ ገለጻዎችና ማብራሪያዎች፣ የጉባኤው ተሳታፊ ዳኞች የማጠናከሪያ ሀሳቦችንና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ቀጥሎ የሚውል ይሆናል።













