ባሕር ዳር፣ መስከረም 25/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት )
“የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎቱን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬም በተለያዩ የሕግ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ገለጻ በማካሄድ ቀጥሏል።
በዛሬው የጉባኤው ውሎ የንግድና የኪሳራ ሕግ ላይ ገለጻ ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ ጴጥሮስ ሲሆኑ፣ በተለይም የኪሳራ ሕግ በዘመናት ውስጥ ያሳየውን የሕግና የፍትሕ እድገት፣ የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ዓላማ እና በአዲሱ የንግድ ሕግ የተካተቱ የሕጉን አጠቃላይ ይዘት በስፋት አብራርተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ እንዳብራሩት፣ የኪሳራ ሕግ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ በሂደት የዳበረ ሲሆን፣ በመጀመሪያ የኪሳራ ሥርዓቶች ትኩረታቸው ባለእዳን መቅጣትና የአበዳሪዎችን ገንዘብ ማስመለስ ላይ ነበር።
የኪሳራ ሕግ በጊዜ ሂደት ባለእዳን ከመቅጣት ወደ ባለእዳው ንብረት በማሰባሰብ፣ በማስተዳደርና ለአበዳሪዎች በፍትሐዊነት በማከፋፈል ላይ ያተኮረ ሥርዓት እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
በተለይም የኪሳራ ሕግ ዘመናዊ እድገት ሀቀኛ ነጋዴዎች በንግድ ሥራቸው በሚያጋጥሟቸው የገንዘብ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት አዲስ የንግድ ሕይወት እንዲጀምሩ እድል የሚሰጥ አቅጣጫ ላይ መድረሱን አቅራቢው አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ በኩልም የ1933 የኪሳራ ሕግ ከቀደምት የሕግ ሥርዓቶች አንዱ መሆኑን ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፣ የ1960 የንግድ ሕግ የ1933 የኪሳራ ሕግን በመተካት የኪሳራ ድንጋጌዎችን በራሱ ውስጥ ማካተቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አዲሱ የንግድ ሕግ በኪሳራ ላይ የተለያዩ የመፍትሔ ሥርዓቶችን ማስቀመጡን ገልጸው፣ በተለይም ቅድመ ጥንቃቄ ዕዳን መልሶ ማዋቀርና መልሶ ማደራጀት ከኪሳራ በፊት የንግድ ድርጅቶች የገንዘብ ችግራቸውን እንዲፈቱ የሚያግዙ ዘመናዊ የሕግ መፍትሔዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ እንዳሉት፣ የኪሳራ ሂደት የባለእዳውን ጥቅም ብቻ ወይም የአበዳሪዎችን መብት ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የብዙ ወገኖችን መብትና ጥቅም የሚነካ ስለሆነ በሕግ የተቀመጡ ሥነ-ሥርዓቶችን በጥንቃቄ መተግበር ይጠይቃል።
በመሆኑም የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ዋና ዓላማ ባለእዳን መቅጣት ብቻ ሳይሆን፣ የአበዳሪዎችን መብት በፍትሐዊነት ማስከበር፣ የባለእዳውን ሀብት በሕጋዊ ሥርዓት ማስተዳደር እና በተገቢው ሁኔታ ለአበዳሪዎች ማከፋፈል እንዲሁም ለሀቀኛ ነጋዴዎች ከኪሳራ በኋላ አዲስ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን አቅራቢው አጽንዖት ሰጥተዋል።
በጉባኤው የኪሳራ ሂደት የዳኝነት ሥልጣን፣ የተለያዩ የሥነ-ሥርዓት ኃላፊዎችና አካላት ሚና፣ የባለእዳው ሀብት ማጣራት፣ የአበዳሪዎች ዕዳ አከፋፈል ቅደም ተከተል እና በመልሶ ማደራጀት ወቅት የሚኖሩ መብቶችና ግዴታዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጓል።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ በተለያዩ የሕግ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የዳኞችን የሕግ ዕውቀትና የዳኝነት አቅም ለማጎልበት የሚያግዙ ስልጠናዎችን፣ ገለጻዎችንና ውይይቶችን በማካሄድ ቀጥሏል።









