ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 310/2018 ላይ ስልጠና ተሰጠ

ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 310/2018 ላይ ስልጠና ተሰጠ

ባህር ዳር፣ መስከረም 24/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

"የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ" በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 20/2019 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ፣ በዛሬ ውሎው፣ በተሻሻለው የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 310/2018 ላይ የዳኞችን የሕግ ማዕቀፍ ግንዛቤያቸውን እና አተገባበርን ለማጠናከር ያለመ ስልጠና ሲሰጥበት ውሏል።

ስልጠናውን የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲኒየር ዳኛ፣ክብርት ዳኛ ወ/ሮ ሳባ አበረ ናቸው።

ስልጠናው በአዋጁ መሠረት በሚነሱ ቁልፍ የሕግ እና የፍትሕ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የመሬት ይዞታ መብቶች፣ የመሬት አስተዳደር እና ምዝገባ፣ የመሬት አጠቃቀም መብቶች፣ ከመሬት ጋር የተያያዙ አለመግባባቶች፣ ማስረጃዎች እና የዳኝነት እና የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊነቶች ላይ ያተኮረ ነው።

የገጠር መሬት ምንነት፣ መሬት የማግኘት መብት፣ የመሬት ውርስ፣ ስጦታ፣ ኪራይ እና ሌሎች የባለይዞታ መብቶች እና የሕጉ አተገባበር በክብርት ዳኛ ወ/ሮ ሳባ አበረ፣ ሰፊ ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ ይገኛሉ።

መሬት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ ያለው፣ ለአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል መተዳደሪያ እና የሕልውና መሠረት በመሆኑ የሚቀርቡ ጉዳዮች በተገቢው ትጋት እና ቅልጥፍና ውሳኔ ሊሰጣቸው የሚገባ ስለመሆኑ በስልጠናው ተነስቷል።

ስልጠናው ዳኞች አዋጁን በተቀራረበ እና በብቃት በመተርጎም እንዲሁም በመተግበር ረገድ ያላቸውን እውቀት እና ተግባራዊ ክህሎት ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ በዚህም ከመሬት ጋር የተያያዙ አለመግባባቶችን ፍትሃዊ፣ ወቅታዊ፣ ሊገመት የሚችል እና ጥራት ያለው መፍትሄ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።

ተሳታፊ ዳኞች በቀረበው ስልጠና ላይ ሀሳብና አስተያይት የሰጡበት ሲሆን፣ ላቀረቧቸው ጥያቄዎችም በአቅራቢዋ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች እና ዳኞች ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጦባቸዋል።

ሁለተኛው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ፣ ነገም በልዩ ልዩ የስልጠና ርእሰ ጉዳዮች ቀጥሎ ይውላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *