ባሕር ዳር፣ መስከረም 22/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ በሦስተኛው ቀን ውሎው የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎችና ገለጻዎችን በማካሄድ ውሏል።
በዕለቱ ከቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል “የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ የፍርድ ቤቶች ሚና” በሚል ርዕስ የቀረበው ሙያዊ ገለጻ ይገኝበታል።
ገለጻውን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር አንችነሽ ሽፈራው ሲሆኑ፣ ፍርድ ቤቶች የሰብዓዊ መብቶች ተግባራዊ ጥበቃ የሚረጋገጥባቸው ዋና ተቋማት መሆናቸውን አብራርተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አንችነሽ እንደገለጹት፣ ሰብዓዊ መብቶች የግለሰቦችንም ሆነ የቡድኖችን መብቶች የሚያጠቃልሉ ሲሆን፣ የሲቪልና የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶችንም ያካትታሉ። እነዚህ መብቶች ተጥሰዋል በሚል ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ቅሬታቸውን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት ሲመጡ ፍርድ ቤቶች መብቶቻቸው እንዲከበሩ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።
ፍርድ ቤቶች በፊታቸው የሚቀርቡ የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳዮችን በሕግ መሠረት በመመርመር የተጣሰ መብት ካለ ተገቢው መፍትሔ እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። በዚህም ሕግን የሚተገብሩ ተቋማት ከሕጋዊ ሥልጣናቸው ውጭ እንዳይሠሩ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ከፍርድ ቤቶች የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች የሀገር ውስጥ ሕጎችን በተግባር ከመተርጎምና ከማስፈጸም ባሻገር ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 መሠረት ተፈጻሚ ማድረግ የሚገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሯ በገለጻቸው፣ የፍትሕ ተደራሽነት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አንዱ መሠረት መሆኑንም አንስተዋል። ሰዎች ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት በአካል በቀላሉ መድረስ፣ የሕግ ድጋፍና የሕግ ውክልና ማግኘት፣ የፍርድ ቤት ሂደቶች ቀላልና ተደራሽ መሆን እንዲሁም የተሰጡ ውሳኔዎች በወቅቱ መፈጸም የፍትሕ ተደራሽነት ዋና መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
“የፍርድ ቤት ሂደት በተራዘመና አድካሚ በሆነ ቁጥር ሰዎች ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት የሚኖራቸው ፍላጎት ይቀንሳል” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አንችነሽ፣ የፍርድ ቤት ሂደቶችን ቀላል፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቶች የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን በሕግ ትርጓሜና አተገባበር ብቻ ሳይወሰኑ፣ ዜጎች የተጣሰ መብታቸውን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት በቀላሉ መድረስ እንዲችሉ የሚያስችሉ የፍትሕ ተደራሽነት ሥርዓቶችን ማጠናከር እንደሚገባቸው በገለጻው ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ “የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል መካሄዱን ቀጥሏል።






