ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ላይ ስልጠና ተሰጠ

ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ላይ ስልጠና ተሰጠ

ባሕር ዳር፣ መስከረም 23/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ “የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 20/2019 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን፣ ዛሬም በተለያዩ የሕግና የፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቱን ቀጥሏል።

በዚህ የጉባኤው መርሐ ግብር ዶ/ር መንበረጸሃይ ታደሰ በፍትሐብሔር ሕግና በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ዙሪያ ለተሳታፊ ዳኞች ሰፊ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዶ/ር መንበረጸሃይ እንደገለጹት፣ ሕጉን ተግባራዊ ማድረግ የዳኝነት ተግባር ሲሆን፣ የፍርድ ቤቶች ዋና ተልዕኮም አለመግባባቶችን በሕግ እና በማስረጃ መሠረት በመፍታት ፍትሕን ማስፈን ነው።

በተለይም የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ የፍትሕ አስተዳደሩ ፍጥነት፣ ወጪ፣ ቀላልነትና ፍትሐዊነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ የሕጉ ይዘት ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚፈጸምበት መንገድም ለፍትሕ አስተዳደር ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

የሕግ አማካሪው እንዳሉት፣ በበርካታ ሀገራት የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውድ፣ የሚዘገይና ውስብስብ መሆኑ በመታወቁ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በዚህም የሥነ-ሥርዓት ሕግ ማሻሻያና በትክክል መተግበር የማሻሻያ ሥራዎቹ ዋና ትኩረት እንደሆነ ገልጸዋል።

በፍትሕ አስተዳደር የሚነሱ ቅሬታዎችና የፍትሕ ጥያቄዎች በአብዛኛው ከሥነ-ሥርዓት ሕግ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ዶ/ር መንበረጸሃይ ጠቁመው፣ ይህም የሕጉን ይዘትና ዓላማ በበቂ ሁኔታ ካለመረዳት ወይም ከአፈጻጸም ድክመት ሊመነጭ እንደሚችል አስገንዝበዋል።

ዳኞች በፍትሕ አስተዳደሩ ውስጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና በመጠቆምም፣ ዳኞች የሥነ-ሥርዓት ፍትሕ አስጠባቂዎች፣ ገለልተኛ የሙግት አመራሮች፣ የማስረጃ ገምጋሚዎች፣ የሕግ ተግባሪዎችና ምክንያታዊ ውሳኔ ሰጪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ዳኞች የቀረበላቸውን ማስረጃና መረጃ በትክክል መመዘን፣ በግልጽና በተጨባጭ ምክንያት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠት እንደሚገባቸው አስረድተዋል። ገለልተኝነትም ከሂደቱ ውጭ መሆን ሳይሆን፣ በሕግ እና በማስረጃ መሠረት በንቃት የሚመራ ሂደትን መጠበቅ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሕግ ሙያ ቀጣይነት ያለው ዕውቀትን የሚጠይቅ መሆኑን ያስገነዘቡት ዶ/ር መንበረጸሃይ፣ ዳኞች በየዕለቱ የሕግ ዕውቀታቸውን ማሳደግና በተለይም የሥነ-ሥርዓት ሕጉን በጥልቀት መረዳት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

“በሕጉ እና በአፈጻጸሙ መካከል ልዩነት ሊኖር ይችላል” ያሉት ዶ/ር መንበረጸሃይ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ሕጉን በትክክል መረዳት ብቻ ሳይሆን በተገቢው መንገድ መፈጸምም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በገለጻው መጨረሻ ተሳታፊ ዳኞች በቀረቡት ሀሳቦች ላይ ጥያቄዎችን፣ ሀሳቦችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን፣ በአቅራቢው ምላሽና ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጦባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *