ባሕር ዳር፣ መስከረም 22/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የዳኝነት ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ አገልግሎትን ማላቅ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ጉባኤ 3ኛ ቀን ውሎ የሴቶች፣ የሕጻናት እና የአካል ጉዳተኞችን ፍትሕ የማግኘት መብት በማስከበር አኳያ የፍርድ ቤቶች ሚና አስመልክቶ ስልጠና ተሰጥቷል።
ስልጠናውን የሰጡት የኢትዮጽያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶች መብት ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ጎጃም አበበ እና በኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች መብት ባለሙያ የሆኑት አቶ አረጋ ሽፈራው ናቸው።
የሴቶች ፣የሕጻናት እና የአካል ጉዳተኞች ፍትሕ የማግኘት መብት፤ ወደ ፍትሕ ተቋማት ያለ አድሎ መቅረብን ወይም ተደራሽነትን፣ እድሜያቸውን፣ ጾታቸው እና የአካል ጉዳታቸውን መሠረት ያደረገ አድሎ ሳይደረግባቸው ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት ማግኘትን፣ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ እና ግንዛቤ ማግኘትን እና ምቹ ችሎቶችን መፍጠርን የሚያካትት መሆኑን በአሰልጣኞቹ ገለጻ ተደርጎበታል።
የሴቶች እና የሕጻናት ፍትሕ የማግኘት መብት አስመልክቶ ስልጠና የሰጡት ወ/ሮ ጎጃም፣ ፍትሕ የማግኘት መብት ሲባል ወደ ፍትሕ ተቋማት ያለ አድሎ መቅረብን ወይም ተደራሽነትን፣ እድሜያቸውን፣ ጾታቸው እና የአካል ጉዳታቸውን መሠረት ያደረገ አድሎ ሳይደረግባቸው ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት ማግኘትን፣ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ እና ግንዛቤ ማግኘትን እና ምቹ ችሎቶችን መፍጠርን የሚያካትት መሆኑን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቶች እነዚሕ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ የሚገባቸው ስለመሆኑ አንስተዋል።
በተጨማሪ ፍርድ ቤቶች የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ፣ ለሕጻናትን መብት ቅድሚያ በመስጠት(best interest of the child) እንዲሁም ለተፈጸሙ ወንጀሎች አስተማሪ የሆነ የቅጣት ውሳኔ መስጠት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ዲክላሬሽን (UDHR)፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውንም አድሎ ለማስወገድ የተደረገ ሥምምነት (CEDAW)፣ የሕጻናት መብት ጥበቃ (CRC) ጨምሮ ሌሎች በሀገራችን የተፈረሙ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ሊሆኑ እንደሚገባ በገለጻቸው አብራርተዋል።
ለአካል ጉዳተኞች የፍትሕ ተደራሽነትን በማረጋገጥ እረገድ የፍርድ ቤቶች ሚናን አስመልክቶ ስልጠና የሰጡት አቶ አረጋ ሽፈራው በበኩላቸው፣አካል ጉዳተኞች የአመለካከት፣ አካላዊ ተደራሽነት፣ የተግባቦት እና ተቋማዊ የሆኑ ተግዳሮቶች የሚገጥማቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የቋንቋ ተግዳሮትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን በመዘርጋት እና የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን በመመደብ እና ተቋማዊ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሚገባቸው መሆኑን አንስተዋል።
የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 568፣ የሕንጻ አዋጅ ቁጥር 1356/2024፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2021 እና ሌሎች የአካል ጉዳተኞችን መብቶች የያዙ የሕግ ማቀፎች ተዳሰዋል።
በዘርፉ ለፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠና መሰጠቱ ለሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን ዳኝነት ፍትሐዊ፣ ተደራሽ፣ ሰብዓዊ መብትን ያከበረ እንዲሆን የሚያስችል እና የዳኞችን ዕውቀት፣ ክህሎትና ሙያዊ አቅም የሚያሳድግ ነው።
"የዳኝነት ተደራሽነት ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ" በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 20/2019 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ፣ ነገም በተለያዩ የስልጠና ርእሶች ቀጥሎ ይውላል።







