ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ከክልሉ የዳኞች ጉባኤ ጎን ለጎን የደም ለገሳ አካሄዱ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ከክልሉ የዳኞች ጉባኤ ጎን ለጎን የደም ለገሳ አካሄዱ

ባሕር ዳር፣ መስከረም 23/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

“የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬም በተለያዩ መርሐ ግብሮች ቀጥሎ ውሏል።

ከጉባኤው መደበኛ መርሐ ግብሮች ጎን ለጎን ዳኞችና ሌሎች የጉባኤው ተሳታፊዎች የደም ልገሳ በማካሄድ የሰው ሕይወትን ለማዳን ያላቸውን ማኅበራዊ ኃላፊነት ተወጥተዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የደም ልገሳውን በማካሄድ ሌሎችም የጉባኤው ተሳታፊዎች ደም እንዲለግሱ አበረታተዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ዳኞች የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል በጉባኤው እየመከሩ እንዳሉ ሁሉ፣ በደም ልገሳም በመሳተፍ ሕይወትን ለማዳን ያላቸውን አለኝታነት ማሳየት አለባቸው።

በተለይም በወሊድ፣ በሕክምና እና በሌሎች አስቸኳይ የጤና ሁኔታዎች ደም የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በደም እጥረት ምክንያት ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ የደም ልገሳ የሰው ሕይወትን ለማዳን ከሚደረጉ ትልልቅ ሰብዓዊ ተግባራት አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

“የሰውን ሕይወት ማዳንን ያህል ትልቅ ነገር የለም” ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ የደም ልገሳ እንደ ማኅበረሰብ ባህል ሊዳብር እንደሚገባው ገልጸዋል።

የደም ልገሳ መርሐ ግብሩ ከደም ባንክ ጋር በመነጋገር መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ ዳኞችም ለዚህ ሰብዓዊ ተግባር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በጉባኤው የተሳተፉ ዳኞችና ሌሎች ተሳታፊዎች የደም ልገሳውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያቀረቡት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ ትላልቅ ጉባኤዎችን የሚያዘጋጁ ተቋማትም የደም ልገሳን እንደ አንድ የመርሐ ግብራቸው አካል ቢያካትቱ በርካታ ዜጎችን ለመታደግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው የዳኞች ጉባኤ ተመሳሳይ የደም ልገሳ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን፣ይህም ከአንድ ጉባኤ ከተደረጉ የደም ልገሳዎች ከፍተኛው መሆኑ ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *