ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በተደራጁ ወንጀሎች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በተደራጁ ወንጀሎች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

ባሕር ዳር፣ መስከረም 22/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

“የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል ለ10 ተከታታይ ቀናት እየተካሄደ ባለው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች 2ኛ ዓመታዊ ጉባኤ፣ በተደራጁ ወንጀሎች ዙሪያ በየደረጃው ለሚገኙ ሁሉም የክልሉ ዳኞች ስልጠና ተሰጧል።

ስልጠናው የጉባኤው ሦስተኛ ቀን የጠዋት መርሃ ግብር ሲሆን፣ የተደራጁ ወንጀሎች ምንነት፣ አይነትና አፈጻጸም፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሳይበር ወንጀል እና ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም የሚሉ ጉዳዮችን ያካተተ ነበር።

ስልጠናውን የሰጡት በድንበር ተሻጋሪና ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍትሕና ወንጀል መከላከል ዘርፍ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ የዳበረ የትምህርትና የሥራ ላይ ልምድ ያላቸው ጠበቃና የሕግ አማካሪ አዲ ደቀቦ (ዶ/ር) ናቸው።

ዶ/ር አዲ በስልጠናቸው፣ የተደራጁ ወንጀሎች ትርፍ ለማግኘት የሚፈጸሙ በመሆናቸው ከሌሎች ወንጀሎች በተለየ መልኩ ሊታዩና ሊመረመሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የተደራጀ የወንጀል ቡድን ለመባል ቡድኑ የራሱ የሆነ መዋቅርና የተለያዩ ሚናዎችን የሚወጡ አባላት ሊኖሩት እንደሚገባ ያብራሩት ዶ/ር አዲ፣ አስተባባሪ፣ መልማይ፣ አጓጓዥ ወይም ሌሎች የወንጀሉን አፈጻጸም የሚያግዙ ሚናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የተደራጁ ወንጀሎች ለፈጻሚዎቹ ያለተገባ ትርፍ ከማስገኘታቸው ባለፈ፣ ሌሎች ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ፣ ይህም የጉዳዩን አደገኛነት እንደሚያጎላው በስልጠናው ተገልጿል።

ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም ከተደራጁ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ጉዳዮች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ ዶ/ር አዲ ገለጻ፣ የተደራጁ ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪ ባሕሪ ሊኖራቸው ስለሚችል ምርመራና ክስ አፈጻጸሙ ልዩ የምርመራ ዘዴዎችንና በሀገራት መካከል የተቀናጀ ትብብርን ይጠይቃል።

በኢትዮጵያም ስለተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በበቂ ሁኔታ መነጋገርና የሕግ አስፈጻሚ አካላትን አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሳይበር ወንጀል ከሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች በተጨማሪ ከውጭ ሀገራት ካሉ ተሳታፊዎች ጋር በትብብር ሊፈጸሙ የሚችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተለይም ሳይበር ወንጀል በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያም በጊዜ ሂደት እየጨመረ የመጣ ስጋት መሆኑን በስልጠናው ተነስቷል።

በመጨረሻም የተደራጁ ወንጀሎችን በተለየ የምርመራና የሕግ አፈጻጸም አቅም መከታተል፣ በተለይም ድንበር ተሻጋሪ ባሕሪ ያላቸውን ወንጀሎች ለመከላከል የሀገራትን ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በስልጠናው ተጠቁሟል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *