ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የፍትሕ አገልግሎትን ቅልጥፍናና ተደራሽነት ለማሻሻል አዳዲስ መርሆዎችን አካቷል” ውብሸት ሽፈራው (ዶ/ር)

“የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የፍትሕ አገልግሎትን ቅልጥፍናና ተደራሽነት ለማሻሻል አዳዲስ መርሆዎችን አካቷል” ውብሸት ሽፈራው (ዶ/ር)

ባሕር ዳር፣ መስከረም 21/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛ ዓመታዊ ጉባኤ ቀጥሎ ውሏል።በጉባኤው የሁለተኛ ቀን ውሎ በአዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ማብራሪያ የቀጠለ ገለጻ ተሰጧል።

በገለጻውም፣አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ የፍትሕ አገልግሎት በጊዜና በወጪ ቆጣቢነት እንዲመራ የሚያግዙ አዳዲስ መርሆዎችንና የሥርዓት ማሻሻያዎችን ማካተቱ ተጠቅሷል ።

ገለጻውን የሰጡት በኮሜሳ የፍትሕ ችሎት ሬጅስትራር የሆኑት የቀድሞው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ውብሸት ሽፈራው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዝግጅት በሀገሪቱ ያሉ ባለሙያዎች የተሳተፋበት ሲሆን፣ በወንጀል ሂደት የሚከሰቱ ጉዳዮችን ከመዳሰስ ባለፈ የሂደቱን ቅልጥፍናና የባለጉዳዮችን መብት የሚያጎለብቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል።

በተለይም የፍርድ ቤት ሂደቶች በግልጽ የጊዜ ገደብ እንዲከናወኑ መደንገጉ ለዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍና የሚሰጠውን ትኩረት ያሳያል። የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍና በጊዜና በገንዘብ ወጪ ሊመዘን እንደሚችል የገለጹት ዶ/ር ውብሸት፣ በሂደቱ ምን ያህል ጊዜና ወጪ እንደሚወስድ በግልጽ መደንገጉ የሕጉ አንዱ ጠንካራ ጎን መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕጉ ከዚህ በፊት በሥነ-ሥርዓት ሕጉ ውስጥ በግልጽ ያልተካተቱ መርሆዎችንም ማካተቱን ዶ/ር ውብሸት ገልጸዋል።

የአፈጻጸም ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ መርሆዎች በሕጉ መካተታቸው ለመብት ተጠቃሚዎች የበለጠ ግልጽና ሰፊ መብት የሚሰጥ መሆኑንም አመልክተዋል።

በሂደቱ የሚሳተፉ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነትም በዝርዝር መቀመጡን ጠቁመው፣ የክርክር መጀመሪያ ሂደቶች፣ የመጥሪያ አዘገጃጀትና አሰጣጥ፣ የማድረስ ኃላፊነት እንዲሁም መጥሪያው በምን ያህል ጊዜ መድረስ እንዳለበት በግልጽ መደንገጉን ገልጸዋል።

ከሕግ ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ እውነትን ማውጣት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ውብሸት፣ ይህንን ዓላማ ለማሳካት የማስረጃ መመዘኛዎች፣ የመከላከያ ማስረጃዎችና የቅጣት ማቅለያ ሁኔታዎች በስፋት መዳሰሳቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል የወንጀል ጉዳዮች የራሳቸው ግልጽ የጉዳይ ፍሰት አስተዳደር እንዲኖራቸው መደረጉን ጠቁመዋል።

ባለጉዳይ በሌለበት ጉዳይ ከመታየቱ በፊትም አማራጭ የመጥሪያ አሰጣጦች መቀመጣቸውን ዶ/ር ውብሸት ገልጸው፣ በዚህም ሂደት ተከሳሽ ባይቀርብም ተጎጂው ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲጠበቅ የተደረገባቸውን ሥርዓቶች አብራርተዋል።

በተጨማሪም ሕጉ ይግባኝና ሰበር ሂደቶችን በተመለከተ አዳዲስ ይዘቶችን ማካተቱን ጠቁመው፣ ይግባኝ ሊባልባቸው የሚችሉና የማይችሉ ጉዳዮች በግልጽ መቀመጣቸውን አብራርተዋል። የይግባኝና የሰበር ሂደቶች ዓላማም በሕጉ ውስጥ በግልጽ መቀመጡን ገልጸዋል።

ዶ/ር ውብሸት እንዳብራሩት፣ የአዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ የሕግ ሂደቱን ግልጽ፣ ቀልጣፋና የባለጉዳዮችን መብት የሚያከብር ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ የሕጉን ድንጋጌዎች በተግባር በትክክል መፈጸም የዳኝነት አገልግሎቱን ቅልጥፍና ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ላይ በቀረበው ገለጻ ተሳታፊዎች ሀሳብና አስተያይታቸውን የሰጡበት ሲሆን፣ ቢብራሩልን ያሏቸውን ጥያቄዎችም አንስተዋል።

በተነሱት ጥያቄዎች ላይ አቅራቢዎቹ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጠዋል።

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ነገም በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ቀጥሎ ይውላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *