ባሕር ዳር፣ መስከረም 21/2019(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
“ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ሁለተኛ ዓመታዊ ጉባኤ ቀጥሎ በሁለተኛ ቀን የጥዋት መርሐ ግብሩ በአዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተካሂዷል።
ለአሥር ቀናት የሚቆየው ጉባኤው በተለያዩ የዳኝነት፣ የፍትሕ አሠራርና የሕግ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን፣ ውይይቶችንና የሙያ ልምድ ልውውጦችን እያካሄደ ይገኛል።
በዛሬው የጉባኤው የጥዋት መርሐ ግብር ላይ የቀረበው ስልጠና የክልሉ ዳኞች አዲሱን የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ፣ የሕጉን ድንጋጌዎች በተግባር በብቃት እንዲያውሉ እና በወንጀል ፍትሕ አሰጣጥ ሂደት ወጥነትና ቀልጣፋነትን እንዲያረጋግጡ ለማስቻል ያለመ ነው።
ስልጠናውን የሰጡት የሕግ ባለሙያ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ እሸቱ ወልደሰማያት ሲሆኑ፣ በስልጠናው የአዲሱ ሕግ ቁልፍ ድንጋጌዎችና ተግባራዊ አፈጻጸማቸው በዝርዝር ቀርበዋል።
በተለይም የወንጀል ምርመራና ክስ አቀራረብ፣ የማስረጃ አቀራረብና ግምገማ፣ የወንጀል ክርክር ሂደት፣ እንዲሁም በወንጀል ፍትሕ ሂደት የሚሳተፉ አካላት መብትና ግዴታዎች ከሕጉ አንጻር ተዳሰዋል።
አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 ዓ.ም ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረውን የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ በመተካት፣ የማስረጃ ሕግንም በወንጀል ፍትሕ ማዕቀፍ ውስጥ በሰፊው የሚያካትት አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ነው።
አዲሱ ሕግ የወንጀል ፍትሕ አሠራሮችን ከሕገ-መንግሥቱ፣ ከወንጀል ሕጉ፣ ከዘመናዊ የሕግ አሠራሮችና ከቴክኖሎጂ እድገቶች ጋር ለማጣጣም ያለመ መሆኑ በስልጠናው ተጠቁሟል።
ስልጠናው ዳኞች አዲሱ ሕግ በዳኝነት ሥራ ላይ የሚያመጣቸውን ተግባራዊ አንድምታዎች በጥልቀት እንዲመረምሩ፣ የሙያ ልምዶቻቸውን እንዲለዋወጡ እና ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ፣ ወጥና መብትን መሠረት ያደረገ የወንጀል ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር የሚያስችላቸውን ሙያዊ አቅም ለማዳበር ዕድል ፈጥሯል። በአጠቃላይ ስልጠናው የክልሉን ዳኞች የሕግ እውቀትና የተግባር አቅም ለማጠናከር እና አዲሱ የወንጀል ፍትሕ ማዕቀፍ በተገቢውና በብቃት እንዲተገበር ለመደገፍ ከሚደረጉ ተከታታይ ጥረቶች አንዱ ነው።










