ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የፍትሕ ሙዚየም ጨምሮ ሌሎች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ሥራዎችን ጎበኙ

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የፍትሕ ሙዚየም ጨምሮ ሌሎች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ሥራዎችን ጎበኙ

ባሕር ዳር፣ መስከረም 21/ 2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ፣ ዘመናዊ፣ ፈጣን፣ ወጪ እና እንግልት ቆጣቢ ለማድረግ የሚስችሉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እያከናወናቸው ያሉ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎች የክልሉን ፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ከማሻሻላቸው በተጨማሪ ለክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ላሉ ተቋማት ምሳሌ መሆን የሚችሉ ናቸው።

የተጀመሩ ተስፋ ሰጭ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎችንም በርካታ የፌደራል እና የክልል ባለሥልጣናት በተለያየ ጊዜ የጎበኟቸው ሲሆን፣ በዛሬው እለትም የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴዎች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመገኘት የለውጥ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የህዝብ እንደራሴዎቹ በጉብኝታቸው፣ የዳኝነት ተደራሽነትን ለማረጋገጥና የፍትሕ ፈላጊውን ማሕበረሰብ ወጪ እና እንግልት የሚቀንሰውን የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች የስማርት ኮርት፣ ኢ-ፋይሊንግ ሲስተም፣ የአንድ ማእከል ዲጂታል አገልግሎት፣ የጥሪ ማዕከል የጎበኙ ሲሆን፣ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን ታሪክ ሰንዶ ለማቆየት፣ ለተማሪዎች እና ተመራማሪዎች ግብአት በመሆን እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀውን እና የምስለ ችሎት ልምምድ ለማድረግ እንዲያስችል ተደርጎ የተገነባውን የፍትሕ ሙዚየም ጨምሮ ምቹ እና ግልጽ ችሎቶችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ዘመናዊ የችሎት ማስቻያ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው መጨረሻ አስተያየታቸውን የሰጡት የሕዝብ እንደራሴዎቹ፣ የተሰራው ሥራ በመሬት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል እና የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *